ብልጽግና እና 'ዩናይትድ ራሺያ' በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና እና 'ዩናይትድ ራሺያ' በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና እና የሩሲያ ገዢ ፓርቲ 'ዩናይትድ ራሺያ' በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የፈረሙት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳና የ'ዩናይትድ ራሺያ' የውጪ ግንኙነት ምክትል ጸሓፊ አንድሪይ ክለሞቭ ናቸው።
ዶክተር ቢቂላ በዚህ ወቅት ብልጽግናና 'ዩናይትድ ራሺያ' በርካታ የሚያመሳስላቸው ነገሮች እንዳላቸው ተናግረዋል።
'ዩናትድ ራሺያ' ብዝሃነትን መሰረት አድርጎ መካከለኛውን ስፍራ ይዞ የሚሰራ መሆኑ ጠቅሰው፤ በተመሳሳይ ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ያለውን ብዝሃነት በተሻለ መልኩ ለማስተናገድ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የብሔር ብዘሃነት፣ ቋንቋና ባህል ያላት አገር በመሆኗ የፖለቲካ ስርዓቱ ይህን ብዛነት ማስተናገድ እንደሚኖርበት ብልጽግና ፓርቲ በጽኑ ያምናል ነው ያሉት።
በዚህ ረገድ ብልጽግና ፓርቲ ከ'ዩናይትድ ራሺያ' ፓርቲ ጠቃሚ ልምዶችን ይቀስማል ብለዋል።
በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው መመሳሰል አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ እድል እንደሚፈጥርም ጨምረው ገልጸዋል።
ዶክተር ቢቂላ አክለውም ሩሲያ ጠንካራ የኢትዮጵያ የልማት አጋር መሆኗንም አስረድተዋል።
የ'ዩናይትድ ራሺያ' ፓርቲ የውጪ ግንኙነት ምክትል ጸሓፊ አንድሪይ ክለሞቭ በበኩላቸው ስምምነቱ 'ዩናይትድ ራሺያ' ከሌሎች የአፍርካ ስመጥር ፓርቲዎች ጋር ለሚኖረው ግንኙነት እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ሁለቱ ፓርቲዎች በቀጣይ በጋራ የሚያከናውኗቸውን ስራዎች ለማቀላጠፍ የሚረዳ መሆኑንም ነው የገለጹት።
'ዩናይትድ ራሺያ' ከጥቂት ወራት በኃላ ከአፍሪካ ታዋቂ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ጉባኤ እያዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል።
ከስምምነት ፊርማው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች የተለያዩ ስጦታዎችን ተለዋውጠዋል።