ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ በ18 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ስምንት መንገዶችን ለማስገንባት ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26 /2013 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በ18 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ ስምንት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ከስራ ተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ ፡፡

ስምምነቱን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ ከአገር በቀል እና ከውጭ አገር የስራ ተቋራጭ ድርጅቶች ስራ አስኪያጆችና ተወካዮች ጋር ተፈራርመዋል፡፡

የሚገነቡት የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች በድምሩ 738 ነጥብ 19 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑ ተገልጿል።

 
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የሰባቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ወጪ በፌዴራል መንግስት የሚሸፈን ነው።

ወጪያቸው በመንግስት የሚሸፈኑት ጫንቃ ጊዳሜ፤ ጎዴ-ሃርጌሌ ኮንትራት ሁለት ኪሎ ሜትር 100-ሃርጌሌ፤ ደብረ ማርቆስ-ደብረ ኤልያስ-ተምጫ-ቁጭ-አየሁ-ዝግም-ቻግኒ ኮንትራት ቁጭ-እምብላ፤ ዱርቤቴ-ቁንዝላ-ገላጎ-መተማ፣ ሎት ሶስት ገላን-ገንደውሃ፤

እንዲሁም ዳንግላ-ጃዊ፤ አዋሽ-ቁልቢ-ድሬዳዋ/ሐረር ኦቨርሌይ ኮንትራት 1፣ አዋሽ-ሜኤሶ፤ እንዳስላሴ-ራማ ገረሁ ሰናይ እንዲሁም ራማ-ገረሁ ሰናይ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች ናቸው።


የጅማ-ጭዳ የመንገድ ፕሮጀክት ደግሞ ከጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድርና በመንግስት እንደሚሸፈን ኢንጂነር ሃብታሙ ገልፀዋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በኅብረተሰቡ የሚነሱ የትራንስፖርት ችግሮችን በማቃለል የምርትና የሸቀጥ ንግድ እንቅስቃሴን ለማቅለል እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።

የመንገድ ፕሮጀክት የአንድ ተቋም ሃላፊነት ብቻ አለመሆኑን የጠቀሱት ኢንጂነር ሃብታሙ ፕሮጀክቶቹን በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ የኅብረተሰቡ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከባለስልጣኑ ጋር ስምምነት የፈረሙት የስራ ተቋራጮች የመንገዶቹን ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ በፍጥነትና በጥራት አጠናቀው ለማስረከብ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

መንገዶቹ የሚገነቡባቸው አካባቢዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ኅብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳቸው የነበሩ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ በማግኘታቸው አመስግነዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት የስራ ተቋራጮች ስራቸውን በወቅቱ እንዲያጠናቅቁ ከጎናቸው በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነትም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበጀት ዓመቱ አጋማሽ በ43 ነጥብ 3 ቢሊዮን  ብር ወጪ 21 የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለመከወን ከአገር ውስጥና ከውጭ የስራ ተቋራጮች ጋር ስምምነት ማድረጉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም