ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ በተለያዩ ሀገራት ለሚሰሩ አምባሳደሮች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መከናወኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26 /2013 (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ ሀገራት ለሚሰሩ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በሀገር ውስጥ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎችን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መከናወኑን አስታወቀ።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው 'ራይዝንግ ኢትዮጵያ' በሚል ርእስ በበይነ-መረብ አማካኝነት መከናወኑም ተገልጿል።

የውይይቱ ዓላማ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅምና ህጋዊ አሠራሮች ላይ የጋራ ግንዛቤ  በመፍጠር ዲፕሎማቶቹ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ማስቻል መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በግብርና፣ ማእድን፣ ቱሪዝም፣ ማኑፋክቸሪንግ እና አይሲቲ ላይ በርካታ እድሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጠቀሱት ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለማበረታታት በርካታ የህግ ማሻሻያዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል ፡፡

ከዚህ ቀደም ለግሉ ሴክተር ዝግ የነበሩ እንደ ቴሌኮም ያሉ ትላልቅ ተቋማት ላይ የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ የሚያስችል የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ ደግሞ ኢንቨስትመንቱን ይበልጥ እያነቃቃው መሆኑን ተናግረዋል።

የኮቪድ ወረርሽኝ በመላው ዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ በፈጠረበት ሁኔታም ውስጥ ሆነን ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡ 

የማእድንና ነዳጅ ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመኝ ውቤ በበኩላቸው የማእድን ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚያስችል አዲስ የማእድንና ነዳጅ ዘርፍ ፖሊሲ መዘጋጀቱንም አንስተዋል።

በመሆኑም በተለያዩ ሀገራት የሚሰሩ ዲፕሎማቶችና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በትኩረት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በእንግሊዝ ሀገር ያሉ ስመጥር ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የተፈጠረውን ምቹ እድል በመጠቀም ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን የተናገሩት ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ናቸው።

የኢትዮጵያን ምርቶች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገበያ በማቅረብ ረገድ የዳያስፖራው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ምርቶች ይበልጥ ለማስተዋወቅም እርስ በርስ ተደጋግፈን መስራት አለብን ነው ያሉት፡፡

የ "ራይዚንግ ኢትዮጵያ" አስተባባሪ ዶክተር በላቸው ተስፋ በተለይ ዲያስፖራው በሚኖርበት ሀገር የኢትዮጵያን እምቅ ሀብት በማስተዋወቅ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ዲያስፖራው የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ በማህበራዊ ሚዲያዎች በተሳሳተ መልኩ የሀገር ገጽታን ለማበላሸት የተከፈተውን ዘመቻ መመከት እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አምባሳደር አባቢ ደምሴ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ አቅም ለማስተዋወቅ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም የዳያስፖራ ተወካዮች የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎችን በማስተዋወቅ ረገድ በትኩረት እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም