ቀጥታ፡

የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊዘረጋለት ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 26 /2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የተገነባው ቡሬ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሚገመት ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር እንደሚዘረጋለት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የቡሬ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቅርቡ ለምረቃ ይበቃል።

ፓርኩ ቢጠናቀቅም ከግንባታው ጋር የታቀደ የኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት እንዳልነበረው ተገልጿል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን የፌዴራል መንግስት ለፓርኩ ኃይል ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ከ80 እስከ 160 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልግ በጥናት መለየቱንም ገልጸዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ ለሚጀምሩ ፋብሪካዎች ከአካባቢው ሀይል ማድረስ የሚያስችል አቅም እንደሌለም ተናግረዋል።

በመሆኑም ከባህርዳርና ከደብረማርቆስ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም ለቡሬ ሁለት አማራጭ ቀርቦ ሲጠና መቆየቱን ገልጸው፤ ከደብረማርቆስ ቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያና ንዑስ ሀይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከዋጋም አንጻር አዋጭ ሆኖ በመገኘቱ ተመራጭ መሆኑን አቶ ሞገስ አስረድተዋል።

92 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ግምታዊ ዋጋ 40 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጹት አቶ ሞገስ፤ "ስራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል" ብለዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም