ቀጥታ፡

ምርት ገበያ 4ተኛውን ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማእከል በጎንደር አቋቋመ

ጎንደር ጥር፣ 26/2013 (ኢዜአ)-የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሀገሪቱ 4ተኛውን ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማእከል በጎንደር ከተማ ማቋቋሙን አስታወቀ፡፡

የግብይት ማእከሉ በነገው እለት በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡

የግብይት ማእከሉ መቋቋም ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ተደራሽ የግብይት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል የምርት ገበያው የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ነጻነት ተስፋዬ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የግብይት ማእከሉ በዋናነት በአካባው በስፋት የሚመረቱትን ሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና አረንጓዴ ማሾን ጨምሮ 12 አይነት የግብርና ምርቶችን ለማገበያየት የሚያስችል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የግብይት ስርአት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

"የግብይት ማእከሉ መቋቋም ከዚህ ቀደም ሻጭና ገዢዎች አገልግሎቱን ለማግኘት አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ይገጥማቸው የነበረውን እንግልትና ወጪ የሚያስቀር ነው" ብለዋል፡፡

ማእከሉ በአንድ ጊዜ 90 የሚደርሱ ሻጭና ገዢዎችን ከ7 እስከ 12 ደቂቃ በፈጀ ጊዜው ውስጥ የማገበያየት አቅም እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ማእከሉ አምራች አርሶአደሮች፣ አቅራቢዎች፣ ላኪዎች፣ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራትና ዩንየኖችን ጨምሮ 357 ቋሚ አባላትና ከ20 ሺህ በላይ ደንበኞችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመላ ሀገሪቱ 23 ቅርጫፎችን ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 19 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ 320ሺህ 140 ቶን የግብርና ምርቶችን ማገበያየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም