የፌቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ተመርቆ ለአገልግሎት ሊበቃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፌቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ተመርቆ ለአገልግሎት ሊበቃ ነው
ባህር ዳር ጥር 25/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ በቀን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር በላይ የተጣራ የምግብ ዘይት ማምረት የሚችል ፋብሪካ በመጭው እሁድ ተመርቆ ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ገለፀ።
ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳምጤ ስማቸው ለኢዜአ እንዳሉት ፋብሪካው 30 ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን ከዘይት በተጨማሪ የሰሊጥ ማበጠሪያና ማቀነባባሪያ ፋብሪካ እንዳለውም ገልፀዋል።
ማርጋሪን፣ ሳሙና፣ ፕላስቲክና ካርቶን ማምረቻ ፋብሪካዎችን እንዳካተተ ጠቅሰው፤ በስድስት ዓመታት ግንባታው ለተጠናቀቀው ፋብሪካ ለግንባታ፣ ለማሽነሪ፣ ለግብዓት ማቅረቢያ ተሽከርካሪና መሰል ወጭዎች ከአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን አስታውቀዋል።
በቀን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ "ቅድሚያ ለሀገር ውስጥ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የማረጋጋት ስራ ይሰራል" ብለዋል።
እሴት የተጨመረባቸውን የሰሊጥና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክም የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
አሁን ላይ እስከ አንድ ሺህ ሰዎችን በቋሚነት የሚቀጥረው ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም ከ3 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ስራ ከመፍጠር ባለፈ ለግብዓት የሚሆኑ የቅባት እህል ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በመግዛት የኢንዱስትሪ ግብርና ትስስር እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በራሱ አቅም የግብርና ምርቶችን የማምረት ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ "በቀጣይ አርሶ አደሩ ልምድን በማካፈል በጥራት አምርቶ እንዲቀርብ ይደረጋል”ብለዋል።
ፋብሪካው ምርቶችን ከአካባቢ ብክለት በፀዳ አግባብ ለማከናወን እንዲችልም አስፈላጊው የማጣሪያ ቴክኖሎጂዎች መገንባታቸውን አመልክተዋል።
ተወዳዳሪና ዘላቂነት ያለው እድገት ለማስመዝገብም የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሚያስፈልጋቸው 10 ሜጋ ዋት ውስጥ 4 ሜጋ ዋት ያህሉ ብቻ እንደገባም አብራርተዋል።
ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታትም በአካባቢው ሰብ ስቴሽን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት መፋጠን እንዳለበትና እስከዚያው ባለው ሃይል ላይ የሚስተዋለው መቆራረጥ እንዲስተካከልም ጠይቀዋል።
ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የምረቃ ስነ-ስርዓትም በመጭው እሁድ ታህሳስ 30/2013 ዓ.ም ታላላቅ መሪዎችና ኃላፊዎች በተገኙበት ይከናወናል ብለዋል።
''ፋብሪካው በትምህርት ካገኘሁት እውቀት ባልተናነስ የተሻለ ልምድ እንድቀስም አስችሎኛል'' ያለው ደግሞ በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ተመርቆ በፋብሪካው የስራ እድል የተፈጠረለት ወጣት ፀሐይነህ አበረ ነው።
ከማሽን ተከላ ጀምሮ የምርት ሙከራ እስኪጀምር ድረስ ከቻይና ከመጡ የዘርፉ ምህራን ጋር በመስራቱ ከፍተኛ ልምድ ማግኘቱንም ገልጿል።
“ለብዙ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር የቻለው ይህ ፋብሪካ በአካባቢዬ በመገንባቱ ደስተኛ ነኝ” ያለችው ደግሞ በዘይት ሙሌት ክፍል እየሰራች የምትገኘው ወጣት እስራኤል አማኑ ናት።
ፋብሪካው በቀጣይም ለሌሎች የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ይችላል ያለችው ወጣቷ ውጤታማ እንዲሆንም በርትታ እንደመትስራ አስታውቃለች።