የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ወደምርት ሥራ መግባት እንዳልቻሉ በደብረ ብርሃን ባለሀብቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ወደምርት ሥራ መግባት እንዳልቻሉ በደብረ ብርሃን ባለሀብቶች ገለጹ
ደብረ ብርሃን ሐምሌ 18/2010 የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ወደ ምርት ሥራ መግባት እንዳልቻሉና ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆናቸውን በደብረ ብርሃን በኢንቨስትመነት ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለጹ። ኢዜአ ካነጋገራቸው ባለሀብቶች መካከል የደብረ ኢጳ ፕሪ ኢንጂነሪይንግ ሶሊሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አይቸው ውሂብ እንደገለጹት ቆርቆሮን ጨምሮ የተለያዩ ብረታ ብረቶችን ለማምረት አስበው በኢንቨስትመንት ሥራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል። ለኢንቨስትመንት ሥራቸው በ79 ሚሊዮን ብር ካፒታል በ1 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ አስፈላጊ ግንባታዎችን ቢያከናውኑም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ፋብሪካው ወደ ማምራት ሥራ አለመግባቱን ተናግረዋል። ችግሩ በፍጥነት እንዲፈታ ከአራት ወር በፊት ትራንስፎርመር እንዲገባላቸው ለኢትጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን የኤሌክትሪክ መስመር ለማዘርጋት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ቢከፍሉም እስካሁን መስመሩ አለመዘርጋቱን ነው የገለጹት። “ከዚህ በተጨማሪ ሪጂኑ ከኢትዮያ ብረታ በረትና ኢኒጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ትራንስፎርመር እንድንገዛ በሰጠን ፍቃድ መሰረት በ750 ሺህ ብር ትራንስፎርመር ብንገዛም የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ስራ ባለመሰራቱ ወደሥራ መግባት ካለመቻላችን ባለፈ የባንክ ወለድ በመክፈል ለኪሳራ ተዳርገናል” ብለዋል። ከሁለት ዓመት በፊት በ40 ሚሊዮን ብር ካፒታል የጀመሩትን የምግብ ዘይት ፋብሪካ ግንባታ ከ4 ወር በፊት ሙሉ በሙሉ ቢያጠናቅቁም በመብራት ችግር ምክንያት እስካሁን ድረስ ወደማምረት ሥራ እንዳልገባ የገለጹት ደግሞ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ የተባሉ ባለሀብት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን ደብረ ብርሃን ቁጥር 2 አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከ15 እስከ 20 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አንዲሰጣቸው ከሁለት ዓመት በፊት ቢጠይቁም እስካሁን ለፋብሪካው የሚያስፈልገውን ኃይል ለማሳወቅ እንኳ ሪጅኑ ፍቃደኛ አለመሆኑን ተናግረዋል። የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ አራት ወር ያለ ሥራ መቆሙን የገለጹት አቶ ጥላሁን ፋብሪካው በወር ከ70 እስከ 90 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ማምረት ቢችልም በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት ወደምርት መግባት ሳይችል መቆየቱን ገልጸዋል። “ለፋብሪካው ግንባታ ከባንክ የወሰድኩትን ገንዘብ በወቅቱ ባለመክፈሌ ለኪሳራ እየተዳረኩ ነው ሲሉም” ባለሀብቱ ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡ የአማይራ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሰው ኃይል አስተዳደር አቶ ጌታቸው ጫኔ በበኩላቸው በአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኪራይ በተመቻቸላቸው ሼድ በ22 ሚሊዮን ብር ካፒታል ፋብሪካ አቋቁመው ለስፖርት ትጥቆችና ካናቲራዎች የሚውሉ ጨርቆችን በከፊል ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል። ፋብሪካው በቀን 1ሺህ 200 ኪሎ ግራም ጨርቆችን በማምረት ጥራት ያለው ካናቲራዎችና የስፖርት ትጥቆችን አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ቢኖረውም በውሃና በመብራት አቅርቦት እጥረት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በቀን 600 ኪሎ ግራም ጨርቅ ብቻ በማምረት ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። ፋብሪካው ማምረት በሚችለው አቅም ማምረት ባለመቻሉ ለኪሳራ እየተዳረገ መሆኑን ገልጸው ችግሩ እንዲፈታ ለሚመለከተው ተቋም ቢያሳውቁም እስካሁን መፍትሄ አለማግኘታቸው በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። በአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ደብረ ብርሃን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የሺጥላ ሙሉጌታ በበኩላቸው 10 ባለሀብቶች ግንባታቸውን አጠናቀው በመብራት ችግር ምክንያት ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከማስተር ፕላኑ ውጪ የተዘረጋ የኤሌትሪክ መስመር እንዲነሳ 121 ሺህ 310 ብር ለኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን ደብረ ብርሃን ቁጥር 2 አገልግሎት መስጫ ማዕከል ክፍያ ቢፈጸምም ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ ሌሎችም ባለሀብቶችም ግንባታቸውን ለማቆም መገደዳቸውን ነው የገለጹት። የመንገድና የውሃ ችግሮችን ለመፍታትም የክልሉ መንግስት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን አቶ የሺጥላ አብራርተዋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን ደብረ ብርሃን ቁጥር 2 አገልግሎት መስጫ ማዕከል የደምበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሀብተየስ ሙሉጌታ በማዕከሉ መስተናገድ የሚችሉ ደንበኞች እስከ 25 ኪሎዋት የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ እስካሁን በኢንዱስትሪ መንደሩ ይህንን አገልግሎት የጠየቀ ባለሀብት አለመኖሩን ነው የተናገሩት። ደንበኞች ለሚፈልጉት አገልግሎት ክፍያ በማዕከሉና በአዲስ አበባ ሪጅን በሁለት ቦታ የሚከፈል መሆኑ ችግሩ ያለበትን ለማወቅ ክፍተት የፈጠረ መሆኑንም አመልክተዋል። ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ የተቋቋመው የአማራ ከልል የኤሌትሪክ አገልግሎት መስጫ ሪጅን በተቀናጀ መልኩ ሥራ በመጀመሩ ችግሩ ትኩረት ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምስራቅ አድስ አበባ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ብርሃኑ ስለጉዳዩ በስልክ ተጠይቀው እንደመለሱት ወደ ዲስትሪክቱ ተመድበው ከመጡ ገና አንድ ወራቸው በመሆኑ ችግሩን በጥልቀት እደማያውቁት ተናግረዋል። መንግስት በቅርቡ ባደረገው መዋቅራዊ ለውጥ በአማራ ክልል ደረጃ ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ከልል የኤሌትሪክ አገልግሎት መስጫ ሪጅን መከፈቱንና በቀጣይ በደብረብርሃ ካለው ማዕከል ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ አስረድተዋል።