ቀጥታ፡

ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሀገራችን የሉአላዊነት መገለጫ ነው… የኢትዮጵያ ባህል ታሪክና ቅርስ አድን ድርጅት

ጎንደር  ጥር 25/2013 (ኢዜአ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሀገራችን የሉአላዊነት መገለጫ በመሆኑ የህዝቡ ድጋፍና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ባህል ታሪክና ቅርስ አድን ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በሀገሪቱ በተመረጡ 26 ከተሞች በመዘዋወር የህዝቡን ተሳትፎ ለማጠናከር የቅስቀሳ ስራ እያካሄደ ነው፡፡ 

የልኡካን ቡድኑን በመምራት በጎንደር ከተማ የተገኙት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ነጮ ወርቁ በአሁኑ ወቅት የህዳሴው ግድብ ግንባታ 78 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

በህዳሴው ግድብ ግንባታ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤በተለይም በ8100 የአጭር የጽሁፍ መልክት እያደረገ ያለውን የገንዘብ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ በተመረጡት ከተሞች በመዘዋወር ህዝቡ ለህዳሴው ግድብ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑንና ከ5 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ጉዞ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

“የልኡካን ቡድኑ በየከተሞቹ የአካባቢውን ወግና ባህል መሰረት በማድረግ እየተዘዋወረ ህብረተሰቡ የመቀስቀስና የማነሳሳት ስራ እየሰሩ ይገኛል” ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው እንደተናገሩት የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ታላቅ ህልም እውን የሆነበት ሜጋ ፕሮጀክት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ዳር እንዲደርስ ህዝቡ በእውቀቱ በገንዘቡና በጉልበቱ ጭምር እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረትና ርብርብ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡

በጎንደር ከተማና አካባቢው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች የሞባይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ በ8100 A ብለው በአጭር ጽሁፍ መልክት በመላክ የህዳሴውን ግድብ በገንዘብ እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በልኡካን ቡድኑ አቀባበል ስነ-ሰርአት ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው የከተማው ነዋሪዎችና እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን ቡድኑ ማምሻውን ወደ ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አቅንቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም