ቀጥታ፡

ሆስፒታሉ የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከል ሂደት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና ሰጠ

ሶዶ፤ ጥር 25/2013 (ኢዜአ) የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሪፈራል ሆስፒታል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በተካሄደው እንቅስቃሴ የላቀ  አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና ሰጠ።

ዛሬ በተዘጋጀው ፕሮግራም  የእውቅና ምስክር ወረቀትና ዋንጫ የተበረከተው ለ30  የጤና ባለሙያዎች፣ ለዩኒቨርስቲው  መምህራንና ሰራተኞች ነው።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ሞላ እንዳሉት ዛሬ ዕውቅና የተሰጣቸው  በሳኒታይዘር ማምረት፣ የተለያ ዩቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የእጅ መታጠቢያ ማሽን በመስራት እና በለይቶ ማቆያ የአምቡላንስ አገልግሎት በመስጠት ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ያበረከቱ  ናቸው።

በቀጣይም የኮሮና ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ የሁሉንም አካላት ጥረትና ተሳትፎ ለማጠናከር  ሆስፒታሉ የጀመረውን የማበረታቻ እውቅና ይቀጥልበታል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር  ታከለ ታደሰ በበኩላቸው ወረርሽኙን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት  እየተደረገ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ኃብትና የሰው ኃይል በመመደብ ከግንዛቤ ማስጨበጥ አንስቶ የምርመራና የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

ባለፉት ወራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በዕለቱ ዕውቅና  ከተሰጣቸው  መካከል የፋርማሲ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር መምህር ታምራት ባልቻ በሰጡት አስተያየት በሙያቸው ለማገዝ  በዩኒቨርሲቲው የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር እንዲመረት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንን  በማስተባበራቸው ያገኙት እውቅና በቀጣይ ለተሻለ ስራ  እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም