የ'ማይስ ቱሪዝም'ን የሚመራ ቢሮ መመስረቱ ኢትዮጵያን ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ተጠቃሚ ያደርጋታል - ቱሪዝም ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
የ'ማይስ ቱሪዝም'ን የሚመራ ቢሮ መመስረቱ ኢትዮጵያን ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ተጠቃሚ ያደርጋታል - ቱሪዝም ኢትዮጵያ
ጥር 25 ቀን 2013 (ኢዜአ) የ'ማይስ' ቱሪዝም'ን የሚመራ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መመስረቱ አገሪቷ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በማስተናገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ቱሪዝም ኢትዮጵያ ገለፀ።
የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ በበኩሉ ኢትዮጵያን ከሌሎች አገሮች በተለየ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ መንገዶችን ተጠቅሞ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ "በሁነቶች ላይ የተመሰረተው 'ማይስ ቱሪዝም' እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ትልቅ ዕድል ቢኖረውም በተለይም በአፍሪካ ከሚደረጉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የኢትዮጵያ የአስተናጋጅነት ድርሻ አነስተኛ ነው" ብለዋል።
በአፍሪካ በየዓመቱ ከ450 በላይ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ ገልጸው፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በደቡብ አፍሪካና በርዋንዳ ከተሞች እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመት ዕቅዷ በየዓመቱ 7 ሚሊዮን ቱሪስቶችን የመሳብ ዕቅድ ማስቀመጧን አስታውሰው፤ "ዕቅዱን ለማሳካት ከተፈጥሮ፣ ከስፖርትና ከመዝናኛ ቱሪዝም ባሻገር የማይስ ቱሪዝም ልማት አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳድሮ ለማሸነፍም ዘርፉን የሚመራና የሚያስተባብር ተቋም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ቢሮው የስብሰባ ማዕከላት እንዲገነቡ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሁነት አዘጋጆች እንዲበራከቱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ለዘርፉ የራሱ መለያ ዓርማ ይፋ መደረጉን ገልጸው፤ የዓርማው መለያ የአገሪቷን ምድረ ቀድምትነትና እንግዳ ተቀባይነት እሴት ማንጸባረቅን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አቶ ስለሺ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ገብረትንሳኤ የተመሰረተው ቢሮ ከሌሎች በተለየ ኢትዮጵያን በቱሪዝም ተወዳዳሪ በሚያደርጉ መንገዶች ላይ በማተኮር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ከነዚህ መካከል ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲናነቷ፣ ከ122 በላይ አገሮች ተደራሽ የሆነ የአፍሪካ ግንባር ቀደም አየር መንገድ ባለቤትነቷ፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧና አገልግሎት የሚሰጡ የሆቴል መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።