የሁነቶች ወይም የማይስ ቱሪዝም ከተሰራበት ብዙ ርቀት ያስኬዳል - ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የሁነቶች ወይም የማይስ ቱሪዝም ከተሰራበት ብዙ ርቀት ያስኬዳል - ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
ጥር 25 ቀን 2013 (ኢዜአ) "የጉባኤ፣ የኮንፍረንስ፣ የማበረታቻ ጉዞና የዓውደ ርዕይ ሁነቶችን ያጠቃለለው 'ማይስ ቱሪዝም' ከተሰራበት ብዙ ርቀት የሚያራምድ ዘርፍ ነው" ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
ማይስ ኢትዮጵያ ጉባዔዎች፣ የጉዞ ማበረታቻዎች፣ ኮንፈረንስና የኤግዚቢሽን ሁነቶችን ያካተተ የቱሪዝም ዘርፍ ነው።
ፕሬዚዳንቷ የማይስ ቱሪዝምን ዘርፍ የሚመራው የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ ምስረታ ላይ ተገኝተው የማይስ ቱሪዝም መለያ ዓርማን ይፋ አድርገዋል።
ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ከባህል፣ ተፈጥሮና ታሪክ ቱሪዝም ፀጋዎች ባሻገር በሁነቶች ዝግጅትም በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል ዕምቅ አቅም እንዳላት ገልጸዋል።
መንግስት በ10 ዓመት ዕቅዱ ቀዳሚ ትኩረት ከሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ቱሪዝም አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የውጭ ምንዛሬ ግኝትና በሥራ እድል ፈጠራ ትልቅ አቅም የሚኖረው ማይስ ቱሪዝም የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ከባህልና ከተፈጥሮ ጸጋዎች በተጨማሪ በአዲስ አበባ የተገነቡ ፓርኮች ለማይስ ቱሪዝም ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥሩ የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤ "ዘርፉ በአግባቡ ከተሰራበት ብዙ ርቀት ያሻግራል" ብለዋል።
"እንግዶችን ለመቀበልና ሁነቶች እንዲከናወኑ አጋር አካላትን በማስተባበር ዘርፉን የሚመራ በቱሪዝም ኢትዮጵያ ስር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መመስረቱም ሌላው ታሪካዊ ዕለት ነው" ብለዋል።
የማይስ ቱሪዝምን ከግብ የማድረስ ጅምር መጠናከር እንዳለበት አመልክተው፤ አካታችና ፈጠራ የታከለበት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ከዚህ ባለፈ እንግዶችን የመቀበል ኢትዮጵያዊ እሴት በማጎልበት ጎብኚዎችን የማስተናገድ ባህል ማዳበር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ቦርድ ሰብሳቢ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ "ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት ምድረ ቀደምት አገር፤ አዲስ አበባም የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ማዕከል ከተማ ናት" ብለዋል።
"በመሆኑም ከሌሎች የቱሪዝም ዘርፎች በተጨማሪ በሁነቶች ላይ የተመሰረተውን የ'ማይስ ቱሪዝም' ለምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ የማዋል ሥራው ትኩረት ይደረግበታል" ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የዓለምና የአህጉር አቀፍ ተቋማት መዲናና ሁነቶችን አስተናጋጅ በመሆኗ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ያቀደች ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን "በምድረ ቀደምት እንገናኝ " የሚል መሪ ሃሳብ ይኖረዋል።
በመርሃ ግብሩ ለዘርፉ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ዕውቅና ተሰጥቷል።