ምክር ቤቱ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አፀደቀ
ጥር 25 / 2013 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር በጊዜያዊነት ስለማገድ ያቀረበውን ማሻሻያና የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ለመደንገግ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን ጨምሮ ሁለት አዋጆችን አፅድቋል፡፡
የህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 32(2)ን በጊዜያዊነት ስለማገድ በቀረበው ማሻሻያ ላይ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቆታል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በተጨማሪ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል፣ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለመደንገግና የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር ሰርዓትን ለመደንገግ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡
ምርጫ ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ አንቀጽ 31(3) በጊዜያዊነት እዲታገድ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረቡ ይታወሳል።
ለዚህ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የምርጫ ወረቀት ልውውጥና ንክኪን ለመቀነስ፣ ባለው የተጣበበ የምርጫ ሰሌዳ ምክንያት ፓርቲዎቹ ፊርማ ለማሰባሰብ በቂ ጊዜ አለማግኘታቸው እንዲሁም አንቀጹ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ያስነሳ መሆኑን በምክንያትነት አንስቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አቡ በርኪ እንደተናገሩት፤ አንቀጽ (32)2 የፓርቲ ተመራጮች የተቀመጠላቸውን ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚደነግግ ሲሆን በማሻሻያው በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ተግባራዊ አይደረግም፡፡
የምርጫ ወቅት የተጣበበ መሆኑና ፊርማ ለማሰባሰብ ያለው ጊዜ አጭር በመሆኑ በአገራዊ ምርጫው ተፈጻሚ እንደማይሆን ሰብሳቢው አብራርተዋል።
የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን በተመለከተም "አገሪቷ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ የተረጋገጠውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ስኬታማ ያደርጋል" ተብሏል፡፡
"አዋጁ ህብረተሰቡ የሚዲያ ነጻነትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርግ ያስችለዋል" ያሉት አቶ አቡ፤ በተጨማሪም በአገሪቷ የተጀመረውን ለውጥ በማስቀጠል የዲሞክራሲ ስርዓቱን የመገንባት ጥረትን ስኬታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን ከነማሻሻያዎቹ መርምሮ በአብላጫ ድምፅ አጽደቆታል፡፡
አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያግዙ አማራጭ መፍትሄዎችን በማጠናከር ፍትህ የማግኘት መብትን እንደሚያግዝ የታመነበት የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር ስርዓት ረቂቅ አዋጅን ምክር ቤቱ መርምሮ አጽድቆታል።
ከዚህ ባሻገር የኢንቨስትመንትና ንግድ ነክ አለመግባባቶችን ከመፍታት አኳያ አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በኢትዮጵያ መንግስትና በደቡብ አፍሪካ መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛ የማስቀረት ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፅድቋል፡፡
የውጭ አገር ስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008ን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡