ቀጥታ፡

በፋይናንስ ስርዓት ላይ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ዝርዝር ጥናት እየተካሄደ ነው- ዶክተር ይናገር ደሴ

አዲስ አበባ ሃምሌ 18/2010 በፋይናንስ ስርዓት ላይ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ዝርዝር ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ተናገሩ። በቅርቡ የተስተዋለው የውጭ አገር ገንዘቦችን ወደ ባንኮች የመመለስ አንዲሁም ህገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎችን የመጠቆም ተግባር ህዝብ ከመንግስት ጎን መቆሙን ማሳያ አንደሆነም አክለዋል። በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሌሎች የፋይናንስ ችግሮች በአምራችና በንግዱ ማህበረሰብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ በስፋት ሲገለጽ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሃላፊነት በመጡ ጥቂት ቀናት ውስጥ ይህን ችግር መቅረፍ ያለመ ውይይት ከንግዱ ማህበረሰብ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተደረጉ ውይይቶች በፋይናንስ ስርዓቱ ላይ የተነሱ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ዝርዝር ጥናት እየተካሄደ ነው። በጥናቱ ውጤት መሰረትም የሚሻሻሉ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከወዲሁ ጠቁመዋል። የተረጋጋ የፋይናንስ እና የኑሩ ሁኔታ እንዲኖር ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍና በወጪ ንግድ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት ሊሰጥ  እንደሚገባ የተናገሩት ዋና ገዥው፤ "በእጃችን ያለውን የውጭ ምንዛሬ ለማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩና የወጪ ምርቶችን ለሚልኩ ባለሃብቶች ቅድሚያ ሰጥተን ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የማድረግ ስራ እንሰራለን ብለዋል። በሌላ ዜና ዜጎች በግለሰቦች እጅ ያሉ የውጭ አገር ገንዘቦች ወደ ባንክ እንዲገቡና ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን በመጠቆም ረገድ ቀና ትብብር እያደረጉ መሆኑን የናገሩት ዶክተር ይናገር፤ "ይህም ህዝቡ ለመንግስት ያለውን ድጋፍ ማሳያ ነው" ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር የሁሉንም ዜጋ ኑሮ የሚጎዳ በመሆኑ ወንጀሉን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ህብረተሰብ ተጠርጣሪዎችን በመጠቆም አሁንም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም