ቀጥታ፡

በሲዳማ የበልግ ማሳ ዝግጅት በ20 ትራክተሮች በመታገዝ እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ፤ጥር 25/2013 (ኢኤአ) በሲዳማ ክልል በተያዘው 2013/14 ምርት ዘመን በልግ ወቅት በዘመናዊ የግብርና መሳሪያ የታገዘ የእርሻ ስራ ለማካሄድ 20 ትራክተሮች መቅረባቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በሎካ አባያ ኦርጋዳ ዲንቱ ቀበሌ እየተካሄደ ያለው በትራክተር የታገዘ የበልግ እርሻ ማሳ ዝግጅት በመስክ ተጎብኝቷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ክፍሌ ሻሾ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት በምርት ወቅት በዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች የታገዘ የእርሻ ስራ ለማካሄድ በባለሀብቶች ተሳትፎ 20 ትራክተሮች ቀርበው ወደ ስራ ገብተዋል ።

በክልሉ በበልግ ወቅት በዋናነት በቆሎና ቦሎቄ አብቃይ በሆኑ ስምንት ወረዳዎች በትራክተሮቹ የእርሻ ስራው እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

የእርሻ ትራክተሮቹ ከግል ባለሃብቶች በኪራይ መቅረባቸውን የገለጹት የቢሮው ምክትል ሀላፊ፤ ትራክተሮቹ የአርሶ አደሩን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በመቆጠብ ምርታማነትን ለማሳደግ የላቀ አስተዋጻ እንዳላቸው አመልክተዋል ።

አሁን ላይ በበልግ ወቅት በበቆሎና ቦሎቄ አብቃይነታቸው በሚታወቁ ሎካ አባያ፣ ቦርቻና ሀዋሳ ዙሪያን ጨምሮ በስምንት ወረዳዎች አርሶ አደሮች በኩታገጠም ተደራጅተው ማሳቸውን በትራክተር በማረስ ለዘር እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በወረዳዎቹ የበልግ እርሻው ከ229 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በ63 ሺህ 188 ሄክታር መሬት ላይ በትራክተር በመታገዝ እየተካሄደ መሆኑን ነው የገለጹት።  

ለምርት ማሳደጊያ የሚሆን ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ፣የቦቆሎና ቦሎቄ ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑን የገለጹት አቶ ክፍሌ፤ ከ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

እርሻን በትራክተር ማረስ በአከባቢው እምብዛም እንዳልተለመደ የገለጹት የሎካ አባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘገዬ ኩሳ፤ ለማሳ ዝግጅት የሚወስደው ጊዜና ወጪ የሚቆጥብ በመሆኑ አርሶ አደሮች ማሳቸውን በትራክተር እያረሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በወረዳው በሚገኙ 22 ቀበሌዎች ሶስት ትራክተሮች ቀርበው እርሻው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁለት ሄክታር ማሳቸው ላይ በቆሎ ለመዝራት በትራክተር ታግዘው የእርሻ ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን የገለጹት የሎካ አባያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገዳሞ ጋልቾ፤ በትራክተር ማረስ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ የሚቆጥብ በመሆኑ ባገኙት ዕድል ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። 

ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ታደሰ ላልማ ከዚህ ቀደም አንድ ሄክታር ማሳቸውን ለዘር ለማዘጋጀት ከስድስት ሰው በላይ በማሰማራት 2 ሺህ 400 ብር ያወጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

ዘንድሮ ማሳቸውን በትራክተር በማሳረሳቸው ወጭያቸው በግማሽ መቀነሱን አርሶ አደር ታደሰ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም