ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የራሱን ማተሚያ ቤት ለማቋቋም ማቀዱን አስታወቀ

ጥር 24/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የራሱን ማተሚያ ቤት ለማቋቋም ማቀዱን አስታወቀ።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ማተሚያ ቤቶች 91 በመቶ የአገሪቱን የሕትመት ፍላጎት መሸፈን እንዳልቻሉ ተጠቁሟል።

8ዐ ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በምስራቅ አፍሪካ ተጠቃሽ የሕትመት ሚዲያ ሊሆን የሚያስችለውን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፏል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሠ እንዳሉት፤ ድርጅቱ የዘመኑን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈተና ተቋቁሞ በምርትና አገልግሎት ጥራቱ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ የማተሚያ ቤት ጉዳይ ቁልፍ ማነቆ ሆኖበታል።

ድርጅቱ በ2022 ዓ.ም በይዘት፣ በገቢና ገበያ፣ በተደራሽነት ልህቀት ማሳካት ከሚፈልገው ግብ ለመድረስ የራሱ ማተሚያ ቤት ማቋቋም እንደሚያስገድደው ገልፀዋል።

ማተሚያ ቤት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ የሕትመት ሚዲያዎች ሁሉ ችግር በመሆኑ ጥራት ያላቸው የሕትመት ውጤቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በውጭ አገሮች እንደሚታተሙ ተናግረዋል።

በመሆኑም የማተሚያ ቤት ጉዳይ አገራዊ ችግር በመሆኑ ዘርፉን ለማዘመን ድርጅቱ በ10 ዓመታት ውስጥ የራሱን ማተሚያ ቤት ለማቋቋም አቅዷል።

ማተሚያ ቤቱን ለማቋቋም የቴክኖሎጂና ቦታ መረጣ ጉዳዮችን አጥንቶ የበጀት ጥያቄ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡንና ምክር ቤቱም በፍላጐት ደረጃ በጎ ግብረ መልስ ስለመስጠቱ አንስተዋል።

“ድርጅቱ የማተሚያ ቤት ማነቆው ከተፈታ የ10 ዓመታት ግቦቹን 50 በመቶ እንዳሳካ ይቆጥረዋል” ያሉት አቶ ጌትነት፤ ዕቅዱን ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት መፈጠሩንም ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህርትና የድርጅቱ የቦርድ አባል ዶክተር አጋረደች ጀማነህ የማተሚያ ቤት ጉዳይ ጥራት ያለውና ተደራሽ የሕትመት ውጤቶችን ለማምረት ወሳኝና የአገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

“ማተሚያ ቤቶች ሲቋቋሙ የወረቀት ፋብሪካና ሌሎች ተጓዳኝ ኢንቨስትመንት ስለሚጋብዙ እንዲቋቋሙ ማድረግ ያስፈልጋል፤ የአገርን ውጭ ምንዛሬ ወጭም ይቀንሳል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የማተሚያ ቤቶች አቅም ማነስና በቂ ማተሚያ ቤቶች አለመኖር ጠንካራ የሕትመት ሚዲያ እንዳይኖርና አንባቢው በተመጣጣኝ ዋጋ የሕትመት ውጤቶችን ገዝቶ እንዳይጠቀም ተግዳሮት ፈጥሯል።

በመገናኛ ብዙሃን በተደረገው ጥናት የኢትዮጵያ የሕትመት ሚዲያውን ኋላቀርና ካለው ህዝብ ጋር ተደራሽ እንዳልሆነ መረጋገጡንገልፀው፤ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ችግሩን መፍታት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ማተሚያ ቤቶች በኢትዮጵያ ያለውን 91 በመቶ የሕትመት ፍላጎት እንደማይሸፍኑ አብራርተዋል።

በዚህም መንግስት በአዲሱ መገናኛ ፖሊሲ ይህን ችግር ለመፍታት ማተሚያ ቤቶችን ማስፋፋት፣ የስርጭት ተደራሽነት እንዲኖር የማተሚያ ቤት ግብዓት ታክስ ቅናሽ እንዲደረግለት በኢንቨስትመንት ማበረታቻነት እንደተመላከቱ ገልፀዋል።

ይህ ፖሊሲ ተፈፃሚ እንዲሆን ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር ባለስልጣኑ መነጋገሩን ጠቁመው፤ “ይህ እንዲሆን ባለስለጣኑ አበክሮ ይሰራል” ሲሉ ተናግረዋል።

የሕትመት ውጤቶች በክልሎች ታትሞ እንዲሰራጭ በርካታ ማተሚያ ቤቶች ስለሚያስፈልጉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የማተሚያ ቤት የማቋቋም ዕቅድ ዕውን መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም