የዶክተር ኢንጅነር አሻሞ ኤረንጎ የቀብር ስነ-ስርአት ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የዶክተር ኢንጅነር አሻሞ ኤረንጎ የቀብር ስነ-ስርአት ተፈጸመ
ሆሳዕና ጥር 24 2013 /ኢዜአ/ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዲዛይን ላይ ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱት የዶክተር ኢንጂነር አሻሞ ኤረንጎ የቀብር ስነ ስርአት በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በሆሳዕና መካነ እየሱስ ማህበረ ምዕመናን አጥብያ ትላንት ተፈጸመ።
ዶክተር ኢንጂነር አሻሞ ከአባታቸዉ ከአቶ ኤረንጎ ጋብጦና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሌንዶ ኤርጅኖ ሐምሌ 25 ቀን 1961 ዓ.ም በሀዲያ ዞን በቀድሞ ኮንተብ ወረዳ በሀዳዬ ቀበሌ ተወለዱ።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሆመቾ አንደኛ ደረጃ የተከታተሉ ሲሆን በየሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሞርሲጦና ዋቸሞ ከፍተኛ ሁለተኛ ጀረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል ።
ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት ከቀድሞ ሶቬት ህብረት በዩክሬን የስኮላርሺፕ የትምህርት እድል በማግኘት ከ 1981 እስከ 1986 የመጀመሪያና የሁለተኛ ድግሪያቸውን በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ በማጠናቀቅ ወደ ሀገራቸው በመመለስ ከ 1987 እሰከ 1990 ዓ.ም በቀድሞው የዲላ እርሻና ቴክኒክ ኮሌጅ አገልግለዋል፡፡
ከመስከረም 1991 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል በመምህርነተና በትምህርት ክፍሉ በሀላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በ1994ዓም ወደ ጀርመን በማቅናት በአድቫንስድ ፕሮፌሽናል ትሬኒንግ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ አጭር ስልጠና ወስደዋል፡፡
ህዝባቸውን በእውቀትና በክህሎት ለማገልገል ከነበራቸው ፍላጎት ከ1995 እስከ 1998 ዓ.ም ሞስኮ ከሚገኘው ሰውዝ ኡራል ስቴት ዩኒቨርስቲ በኤሌትሪካል ፓወር ኢንጂነሪንግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተከታታለዋል፡፡
ወደ ሀገራቸው በመመለስ ከ1999 እስከ 2003 ዓም በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም በመክፈት በረዳት ፕሮፌሰርነትና በትምህርት ክፍሉ በሀላፊነት አገልግለዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ መመስረትን ተከትሎ ከ2003ዓም ጀምሮ በዩኒቨርስቲው በተጠባባቂ ፕሬዝዳንትነትና በዋናነት በአካዳሚክና ምርምር ፕሬዝዳንትነት ለተከታታይ ስድስት ዓመት አገልግለዋል።
የሀገሪቱ ህልውና በሆነው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዲዛይን ዙሪያ በሙያቸው እንዲያግዙ ከመንግስት የቀረበላቸውን ጥያቄ በመቀበል በግድቡ ግንባታ ዲዛይን ስኬታማነትና ውጤታማነት ላይ አስተዋጻ ማድረጋቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ዶክተር ኢንጂነር አሻሞ ኤረንጎ ሀላፊነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው በመልቀቅ በዩንቨርስቲው በኢንጀነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በመምህርነት እያገለገሉ የነበሩ ሲሆን ጥር 21 ቀን 2013ዓም በድንገት በ53 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በሆሳዕና መካነ እየሱስ ማህበረ ምዕመናን አጥበያ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት ስርዓተ ቀብራቸዉ ትላንት ተፈፅሟል።
ዶክተር ኢንጂነር አሻሞ ኤራንጎ የሶስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።