የሽሮሜዳ የባህል አልባሳት የገበያ ማዕከል ተመረቀ

92

አዲስ አበባ ጥር 23/2013 (ኢዜአ) የሽሮሜዳ የባህል አልባሳት የገበያ ማዕከል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ፡፡

ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ማዕከል ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ይፈጠራል ተብሏል።

የሽሮሜዳ ባህላዊ አልባሳት መሸጫ ገበያ ማዕከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው ተመርቆ ለአገልግሎት  ክፍት የሆነው።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት የሽሮሜዳ  የባህል  አልባሳት  መሽጫ  የገበያ ማዕከል ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጠር ነው።

ማዕከሉ ዓለምአቀፍ እውቅና ካለው እንጦጦ ፓርክ ጋር ቅርበት ስላለው በርካታ የቱሪስት ፍሰት እንደሚኖርም ምክትል ከንቲባዋ ገልፀዋል፡፡

በአገሪቱ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየው  ባህላዊ  አልባሳትን  ለማስተዋወቅና  ቱሪስቶችን  ለመሳብ በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲያቀርቡ ምክትል ከንቲባዋ አሳስበዋል፡፡

''የባህል ልብስ ሲነሳ ሽሮሜዳ፤ ሽሮሜዳ ሲነሳ የባህል ልብስ የማያስታውስ የለም'' ያሉት የጉለሌ ክፍለ  ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አባወይ ዮሐንስ በሽሮ ሜዳ አካባቢ ላሉ ወጣቶች የባህላዊ አልባሳት ገንብቶ ማስረከብ ትርጉሙ ትልቅ ነው ብለዋል።

የባህል አልባሳት መሸጫ ማዕከሉ እንደዚህ እውቅና ሳይሰጠው የሽሮ ሜዳ ባህላዊ አልባሳት ሰሪዎች በትንሽ ዋጋ ባህሉን ሲያስተዋውቁ  እንደቆዩም አስታውሰዋል።

በገበያ መሰረተ ልማት አለመኖር በርካታ ባለሙያዎች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲኖር አድርጎ እንደነበርም ጠቁመዋል።

የገበያ ማእከሉ 380 የመሸጫ ቦታዎችን የያዘ ሲሆን ከክፍለ ከተማው ለተውጣጡ ከ980 በላይ ስራ-አጥ ወጣቶችና ሴቶች ፤

እንዲሁም በመንገድ መሰረተ ልማት ከመስሪያ ቦታቸው ለተፈናቀሉ 153 ዜጎች መከፋፈሉን ጠቁመዋል።

የገበያ ማዕከሉ የክፍለከተማውን የባህል አልባሳት አምራችና ሸማች ትስስርን ለማሻሻል ይጠቅማል ብለዋል።

በሽሮሜዳ ባህላዊ አልባሳት መሸጫ ማዕከል የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችና ሴቶች በበኩላቸው በተደረገላቸው ነገር መደሰታቸውና የተሻለ ስራ ለመስራት መዘጋጀታቸው ገልፀዋል፡፡

አቶ በሃይሉ እሸቴ ባገኙት ዘመናዊና የመሸጫ ማዕከል ከእንጦጦ ፓርክ የሚመጡ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን በጥሩ ሁኔታ ለማገልገል ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

ወይዘሮ መሰረት ሳህሉ በበኩላቸው የልማት ተነሺ ሲሆኑ እድሉን በማግኘታቸው በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም