በግማሽ አመቱ ከ22 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል -- የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ

26

አዳማ ጥር 23/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮ 2013 በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወር ከ22 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወር የዕቅድ አፈጻጸም ትላንት በአዳማ ከተማ ገምግሟል።

የቢሮው የታክስ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ረታ በወቅቱ እንደገለጹት ቢሮው በበጀት ዓመቱ 43 ቢሊየን ብር ለመሰብሳብ አቅዶ እየሰራ ነው።

በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት  24 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 22 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ 94 በመቶ መሳካቱን ተናግረዋል።

በግማሽ አመቱ የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ከ44 ሺህ በላይ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ገቢ ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ህጋዊ ያልሆኑ 50 ሺህ ነጋዴዎችን ወደ ግብር ስርዓት ማስገባት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የአምስትና የ10 ዓመት ዕቅድ ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው በ10 ዓመት የልማት ዕቅድ 88 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በቢሮው የኮርፖሬት ስራዎች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ውዴ ቴሶ በበኩላቸው "ሁሉም አመራርና ሰራተኛ የተሰጣቸውን ተግባር  በአገልጋይነት ስሜት በማከናወናቸው በግብር አሰባሰቡ አበረታች ወጤት ሊመዘገብ ችሏል" ብለዋል።

በመድረኩ የመጀመሪያውን ግማሽ አመት የገቢ ስብሰባ አፈጻጸም በመገምገም በቀሪው ስድስት ወር የተሻለ በመስራት በበጀት አመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው በላይ ገቢ ለመፈጠም አቅጣጫ መያዙን አመልዕክተዋል።

ለተግባራዊነቱ እስከ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎችን በማሳተፍ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም