የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች በዓል በዓለም ጎልቶ እንዲታወቅ ድጋፍ ይደረጋል- አቶ አገኘሁ ተሻገር

50

ባህርዳር ጥር 23/2013 (ኢዜአ) በየዓመቱ ጥር 23 ቀን የሚከበረው የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች በዓል በዓለም ጎልቶ እንዲታወቅ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

81ኛው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል ዛሬ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት በክልሉበየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት አንዱ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች  ማህበር ነው፡፡

የአዊ ህዝብ ከኢትዮጽያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወንድሞቹ ጋር በመሆን የፋሺስት ኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ለማንበረከክ አድዋ ላይ ተጋድሎ ባደረጉበት ወቅት ፈረሶች ያበረከቱትን ውለታ ለማስታወስ በዓሉ የሚከበር መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል

"የማህበሩ አባላት የአባቶቻቸውንና የአያቶቻቸውን ታሪክ ጠብቀው በማቆየት ዛሬ 81ኛው የፈረሰኞች በዓል በድምቀት እንዲከበር ማድረጋቸው ያስመሰግናቸዋል" ብለዋል።

በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።፡

በቀጣዩ ዓመት በዓሉ በድምቀት የሚከበር በመሆኑ ቱሪስቶች መጥተው እንዲጎበኙት   ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ በዓሉን የማስተዋወቅ ሥራ ተግተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

"የአዊ ህዝብ በሥራ ወዳድነቱና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በማቆየት በኩል በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው" ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ ህዝቡ የሚታወቅበትን ተግባር አስጠብቆ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

 "በዓሉ እብሪቱ ጫፍ የደረሰው የህዋሃት አጥፊ ቡድን በህግ ማስከበር ዘመቻ ዳግም ላይመለስ በተወገደበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል" ያሉት ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን ናቸው፡፡

የአዊ የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች በዓል የአባቶቻችንን የቀደመ ገድል በሚያስታውስ መልኩ በየዓመቱ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እየተከበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡

"በዓሉ የበለጠ ጎልቶ ለቀጣዩ ትውልድ በባህላዊ ቅርስነት እንዲተላለፍና ለቱሪስት መስህብነት እንዲውል ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል፡፡

"የፈረስ ውለታ ተዘርዝሮ አያልቅም" ያሉት ደግሞ የአዊ ዞን የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች  ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ጥላዬ አየነው ናቸው።

"ፈረስ ጣሊያንን ከሀገራችን ለማስወጣት ከከፈለው ተጋድሎ ባለፈ ለአዊ ህዝብ ለእርሻ ፣ ለእቃ ማጎጎዣ፣ ለለቅሶና ለባህል ማድመቂያ እያገለገለ የሚገኝ ባለውለታችን ነው" ብለዋል፡፡

በዓሉ በፈረስ ጉጉስ፣ በፈረስ ሸርጥ ፣ በፈረስ ግልቢያና በሌሎች ትርኢቶች በድምቀት ተከብሯል።

በ1933 ዓ.ም. የተመሰረተው የአዊ ዞን የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር በአሁኑ ወቅት ከ53 ሺህ በላይ አባላት አሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም