ባለፈው ዓመት የጀመርነው አቮካዶን እና ፓፓያን የማዳቀል ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተከወነ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

65

ጥር 23 /2013 (ኢዜአ) “ባለፈው ዓመት የጀመርነው አቮካዶን እና ፓፓያን የማዳቀል ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተከወነ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።

አቮካዶን እና ፓፓያን የማዳቀል ሥራው በሚቀጥለው ዓመት ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን የማድረስ ትልቅ አቅም ማሳየቱንም በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ”ከግብርና ዘርፍ ማግኘት የሚገባንን ሃብት ለማግኘት አቅማችንን አሟጠን መስራት ይኖርብናል” ማለታቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ጤፍ በማምረት የሚታወቁ የሸዋ አካባቢዎች አሁን በስፋት አቦካዶ ማምረት መጀመራቸው ገልጸው፤ አቮካዶ ከአመታት በኋላ የቡናን ያህል በወጪ ንግድ ገቢ የማስገኘት አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

አቮካዶ በኢትዮጵያ ምርት የሚሰጠው በከፍተኛ ደረጃ የሚፈለግበት ወቅት ላይ በመሆኑ ትልቅ የገበያ ዕድል እንዳለው መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም