ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያዋስናት ፈጋግ ድንበር ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ኬላ ሥራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያዋስናት ፈጋግ ድንበር ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ኬላ ሥራ ጀመረ
ጋምቤላ፤ ጥር 22/2013 (ኢዜአ ) የኢሚግሬሽን ፣ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያዋስናት የጋምቤላ ክልል ፈጋግ ድንበር የመጀመሪያው ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ኬላ ዛሬ በማስመረቅ ሥራ ጀመረ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክታር አቶ ሙጂብ ጀማል በምረቃ ስነ- ስርዓቱ ወቅት እንዳሉት የመቆጣጠሪያ ኬላው የሁለቱ ሀገራትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል።
በተለይም በአካባቢው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርንና አሁን ላይ የሀገራት ስጋት የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ጭምር ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተለ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ኤጀንሲው ከ2012ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ ጠረፋማ አካባቢዎች ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ኬላዎችን በማቋቋም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርንና ፍልሰትን ለመቆጣጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዕለቱ የተመረቀው የመቆጣጠሪያ ኬላ ኤጀንሲው ችግሩን ለመግታት እያደረገ ያለው ጥረት አካል መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
አስከፊ የሆነውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመግታት ዘንድሮ ብቻ ጋምቤላን ጨምሮ ሀገሪቱ በምትዋሰንባቸው አራት ቦታዎች ዘመናዊ የመቆጣጠሪየ ኬላ መክፈቱን የተናገሩት ደግሞ የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታመሩ ገንቦቶ ናቸው።
ይህም በሀገሪቱ ያሉት መቆጣጠሪያ ኬላ ቁጥር ወደ 16 ከፍ እንዳደረገው ጠቁመው በቅርቡ ቤኒሻንጉልን ጨምሮ በሌሎች ጠረፋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጨማሪ ኬላዎችን ለመክፍት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ የፍልሰት ቁጥጥር ኃላፊ ሚስተር ማሌንጎ ሞንጋ በበኩላቸው ሰፊ የሆነው የአፍሪካዊያን ፍልስት የሚካሄደው በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ነው ብለዋል።
ዛሬ የተመርቀው የመቆጣጠሪያ ኬላ በአካባቢው የሚታየውን የሰዎች ዝውውር፣ የኮሮና ቫይርስንና ሌሎች ድንበር ዘለል ችግሮችን ለመከላከልና ለሰዎች ድህንነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ተወካይ አቶ አኳይ አቡቲ ኤጀንሲው በክልሉ ያቋቋመው መቆጣጠሪያ ኬላ በክልሉ ጠረፋማ አካባቢ ያለውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በመግታት ረገድ የላቀ ጠቀሜታ ይኖራዋል ብለዋል።
ኤጀንሲው ለጀመራቸው ሥራዎች መቀናት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሰታውቀዋል።
የመቆጣጠሪያ ኬላው በኮምፒዩተርና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች የተደራጁ የቢሮና የሰራተኞች መኖሪያ ክፍሎች እንዳሉት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።