የስደተኞችን የኃይል ፍላጎት በአማራጭ የኃይል ምንጭ ለመተካት የሚያስችል የ120 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የስደተኞችን የኃይል ፍላጎት በአማራጭ የኃይል ምንጭ ለመተካት የሚያስችል የ120 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
ሽሬ እንዳስላሴ ሐምሌ 17/2010 በተፈጥሮ የደን ሃብት ላይ የተመሰረተውን የኤርትራውያን ስደተኞች የኃይል ፍላጎት በአማራጭ የኃይል ምንጭ ለመተካት እንዲቻል የ120 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊሆን ነው። ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የፕሮጀክት ክትትልና ግምገማ ክፍል ኃላፊ አቶ ፍስሃ መሰረት ፕሮጀክቱን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ እንዳሉት፣ ፕሮጀክቱ የተቀረጸው የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት ሲባል በደን ሀብት ላይ ይድርስ የነበረው ውድመት ለመታደግ ነው። በፕሮጀክቱም ስደተኞች ለመኖርያ ቤታቸው ከፀሐይ ብርሃን የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን በመጠልያ ጣቢያዎቹ ዙርያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የኃይል አቅርቦቱን እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተገለጸው ከአውሮፓ ህብርት በተገኘው ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚገነባው የኃይል አማራጭ ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚደረገው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በሚገኙ የአዲ- ሀሩሽ፣ የማይ ዓይኒ፣ የህጻጽና የሽመልባ የኤርትራውያን መጠልያ ጣቢያዎች ውስጥ ነው። ፕሮጀክቱ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ግንባታ፣ የኤሌክትሪክ መብራት መዘርጋት ሥራና በነፍስ ወከፍ የስደተኞች መኖርያ ቤት የኃይል ፍላጎትን ማሟላት እንደሚያካትት አቶ ፍሰሀ አስረድተዋል። በፕሮጀክቱ ስደተኞቹ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የኃይል አማራጭ እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን ገልጸው ፕሮጀክቱን በኃላፊነት ወስዶ የሚያሰራው " ዞአ " የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑ ተመልክቷል። በድርጅቱ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ በረከት ጎዲፋይ ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ በአዲ ሀሩሽ መጠልያ ጣቢያ ተሞኩሮ ውጤታማ በመሆኑ ወደ አራቱ የስደተኞች መጠሊያ ጣቢያ ለማዳረስ መታቀዱን ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታ በመጪው ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚጀመርና በቀጣይ ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል። በአዲ ሀሩሽ የኤርትራውያን መጠልያ ጣቢያ በሙከራ ደረጃ ቀደም ብሎ የተጀመረው አማራጭ ኃይል አዋጭና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እያገኙበት መሆኑን የገለጸው በመጠለያ ጣቢያው የሚኖረው ኤርትራዊ ስደተኛ ወጣት ኤርሚያስ ሀጎስ ነው። በኢትዮጵያ በሚገኙ 27 የስደተኛ መጠሊያ ጣቢያዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስድተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ዋና መሥርያ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።