የ'ኦንላይን' ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ነገ በይፋ ይጀመራል

ጥር 21/2013 (ኢዜአ) የንግድና ኢንዳስትሪ ሚኒስቴር የ'ኦንላይን' ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት የአሰራር ስርዓትን ነገ በይፋ እንደሚጀመር ገለፀ።

በኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት የአሰራር ስርዓት ከ3 ሺህ በላይ በሆኑ ደንበኞች የሙከራ ትግበራ ተካሂዶበታል።

ሚኒስቴሩ አገልግሎቱን አስመልክቶ ለንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዩችና የሚዲያ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ አድርጓል።

የሚኒስቴሩ የጥራት፣ ንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አሰፋ የኦንላይን አገልግሎቱ ኢትዮጵያን አገራዊ የዳታ ቤዝ ማዕከል ባለቤት በማድረግ በንግዱ ዘርፍ የሚያጋጥሙ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ለመስጠት 11 ቀናት ይወስድ የነበረውን ወደ አምስት ቀናት በመቀነስ የደንበኞችን እንግልት ለማቃለልም ያስችላል።

የኦንላይን አገልግሎቱ የንግዱን ማኅበረሰብ እንግልት በመቀነስ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎቱን እንደሚያሳድግ የሚኒስቴሩ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ጸጋው በለጠ ገልፀዋል።

የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት የአሰራር ስርዓት የንግድ ምዝገባና ስራ ፈቃድ ለማውጣት ያጋጥሙት የነበሩ እንግልቶችንም በእጅጉ ይቀንሳል ተብሏል።

አዲሱ ቴክኖሎጂ የዘርፉን የአሰራር ስርዓት ቀላል፣ ቀልጣፋና ተደራሽም ያደርጋል።

ሚኒስቴሩ ነገ የሚያስመርቀው የቀጥታ የበይነ መረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት አገሪቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በንግድ ስራ ፈቃድ አመቺነት ያላትን ደረጃ በማሻሻል፣ በንግድ ስራ መጀመር ሂደት፣ በገጽታ ግንባታና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተመራጭ ያደርጋታል ተብሏል።

የበይነ መረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ ነገ ጥር 22 ቀን 2013 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል በይፋ ይመረቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም