ምርት ገበያው አራተኛውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል በጎንደር ሊከፍት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምርት ገበያው አራተኛውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል በጎንደር ሊከፍት ነው
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አራተኛውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል በጎንደር ከተማ ሊከፍት መሆኑን ገለጸ።
ምርት ገበያው የ2013 በጀት ዓመት አጋማሽ የአፈጻጸም ሪፖርቱን አቅርቧል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ እንደገለጹት በግማሽ ዓመቱ 320 ሺህ 140 ሜትሪክ ቶን ምርት በ19 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል።
በተጠቀሰው ጊዜ 140 ሺህ ቶን ሰሊጥ እና 10 ሺህ 592 ቶን አኩሪ አተር ማገበያየቱንም ገልጸዋል።
ነጭ የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦለቄና ፒንቶ ቢን ወደ ዘመናዊ የግብይት መድረክ በመግባታቸው ምርት ገበያው የሚያገበያያቸው ምርቶች ቁጥር 12 ደርሷል።
ጥጥ፣ ቅመማ ቅመምና ጥራጥሬን ጨምሮ ዘጠኝ ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ግብይት ለማስገባትም የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል።
መሰረተ ልማት በማስፋፋት ረገድ በቡሌ ሆራ እና በመቱ የተገነቡትና እያንዳንዳቸው 150 ሺህ ሄክታር የሚይዙ መጋዘኖች ተጠናቀዋል።
በሌላ በኩል ምርት ገበያው ተቋማዊ አቅሙን በማሳደግ ተደራሽነቱን በማስፋፋት ከሃዋሳ፣ ሁመራና ነቀምት የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት በተጨማሪ አራተኛውን የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከል በጎንደር ከተማ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚከፍት ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
የግብይት ማዕከሉ መከፈት የዘመናዊ ግብይት አገልግሎቱን ለአርሶ አደሩ፣ ለአቅራቢዎች፣ ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎችና ላኪዎች ካሉበት ሆነው ግብይት እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ብለዋል።
በአዳማ እና በጅማ ከተሞችም ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከላት ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን በሚዛን ተፈሪና በቴፒ አዳዲስ ቅርንጫፎች ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።