ቀጥታ፡

የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማዘመን በአቅም ግንባታና በገበያ ትስስር ዘርፍ እየሰራሁ ነው - የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር

ጥር 21/2013 (ኢዜአ) የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማዘመን በሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ እየሰራሁ ነው ሲል የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር ገለፀ።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ጌታሁን እንደገለፁት ማኅበሩ የሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን ለአገሪቷ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ሚናውን እየተወጣ ነው።

ዘርፉን ዘመናዊ ለማድረግም የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በሶስት መንገዶች በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

እነዚህም የዘርፉ ድምጽ መሆን፣ አቅም ግንባታና የገበያ ትስስር ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

የዘርፉን ክንውኖች ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በግብዓትነት በማቅረብ ፖሊሲዎች መሻሻልና መለወጣቸውን እንዲሁም ዘመናዊ አሰራሮች መተግበራቸውን ገልጸዋል።

የዘርፉ ተዋናዮች ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚያቀርቡበትን አቅም ለመገንባት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አጋርነት መፍጠራቸውንም እንዲሁ።

ማኅበሩ ከዓለምአቀፉ የዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበር ባገኘው እውቅና መሰረት የፊያታ /ኤፍ.አይ.ኤ.ቲ.ኤ/ ዲፕሎማ በአትዮጵያ በብቸኝነት እየሰጠ መሆኑንም ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ከጀርመን የቴክኒክ ድርጅት ጋር በመተባበር ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቁ 80 ወጣቶች የስድስት ወራት ስልጠና በነጻ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ገለጻ ወጣቶቹ ዘርፉን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ክልል ዕቃ አስተላላፊ ኩባንያዎች /አር.ኤ.ኤም.አይ/ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሰላህዲን ከሊፋ በበኩላቸው መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት እያደገ ቢሆንም ለአገሪቷ በሚስማማ መልኩ ለመተግበር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘርፉ አገሪቷን በማስተዋወቅ፣ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት፣ ለስራ ፈጠራ፣ ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የማይተካ ሚና እንዳለውም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም