ኢትዮጵያና ሱዳን ችግሮቻቸውን በሠላማዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሱዳን ችግሮቻቸውን በሠላማዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል - ምሁራን
አዲስ አበባ ጥር 21/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ሱዳን ባላቸው ወዳጅነትና መልካም ጉርብትና ከድንበር ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን አለመግባባት በሠላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባቸው ምሁራን ተናገሩ።
አገራቱ የአፍሪካ ኅብረት የድንበር ክርክርን ለመፍታት ያስቀመጠውን አሰራር እንዲጠቀሙም መክረዋል።
የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ማካለል ጉዳይ 118 ዓመታትን አስቆጥሯል።
እ.አ.አ 1902 ቻርልስ ጉዊን የተባለ እንግሊዛዊ የሁለቱን አገራት ድንበር በማካለል ሪፖርት አቅርቧል።
ይሁንና ጉዊን የድንበር ማካለሉን ያደረገው ያለ ኢትዮጵያ መንግስት እውቅና በመሆኑ ኢትዮጵያ ሪፖርቱን ውድቅ አድርጋዋለች።
ኢትዮጵያና ሱዳን እ.አ.አ 1972 በተፈራረሙት የሀሳብ ልውውጥ ስምምነት መሰረት በድንበር ጉዳይ የመፍትሔ ሀሳብ ላይ እስኪደርሱ አሁን ያለው ድንበር ተከብሮ እንዲቆይ መስማማታቸውም ይታወሳል።
ሱዳን በስምምነቱ ተከብሮ እንዲቆይ የተባለውን የድንበር ነባራዊ ሁኔታ ጥሳ የኢትዮጵያን መሬት መያዟንና ይህም የተፈረራሙትን ስምምነት የጣሰ መሆኑን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
ኢዜአ በጉዳዩ ዙሪያ ምሁራንን አነጋግሯል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤምራተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ኢትዮጵያና ሱዳን ለዘመናት የዘለቀ ወዳጅነትና ትስስር እንዳላቸው አውስተዋል።
ትብብርና መተጋገዝ መገለጫው የሆነው የአገራቱ ወዳጅነትና ታሪካዊ ግንኙነታቸው በበጎ እንደሚነሳም ጠቅሰዋል።
በታሪክ የኢትዮጵያና የሱዳንን ድንበር ጉዳይ ለመፍታት የተጀመሩ ጉዳዮች በአገራቱ መንግስታት መለዋወጥ እልባት ሳያገኙ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
"ሱዳን የፈጸመችው ድርጊት የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮልኛል" በሚል ያደረገችው እንደሆነም ፕሮፌሰር ባህሩ ተናግረዋል።
ችግሩን በመከባበርና በመነጋገር ብቻ መፍታት እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
የመልክዓ ምድር ተመራማሪውና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ሙላቱ ውብነህ ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳዩን የሚያስተሳስሯቸውንና የሚያዛምዷቸውን ጉዳዮች በማስቀደም መፍታት ይችላሉ ይላሉ።
የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት የድንበር ጉዳይ አለመግባባቶችን በውይይትና በድርድር መፍታት የሚያስችላቸውን መርሃ ግብር እ.አ.አ 2007 ይፋ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
አገራቱ በመርሐ ግብሩ መሰረት በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረው መፍትሔ ላይ መድረስ እንደሚገባቸው ፕሮፌሰር ሙላቱ ገልጸዋል።
በድንበሩ ጉዳይ ወደ ውይይት የሚገባ ከሆነ በዚያ አካባቢ የሚኖሩ የአገራቱን ዜጎች ተወካዮች ያሳተፈ መሆን አለበትም ብለዋል።
በቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ የስልጣን ዘመን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የነበሩት የጎንደር ነዋሪ አቶ ባዩ በዛብህ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያና ሱዳን በመንግስታት ደረጃ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸውንና ከውይይቶችም ዘላቂ መፍትሔ እንዳልተገኘ አስታውሰዋል።
አገራቱ የድንበሩን ጉዳይ ለመፍታት መነጋገርና መወያየት እንደሚገባቸውም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እንደምታደርግ በተደጋጋሚ ጊዜ መግለጿ ይታወቃል።