ትግራይን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ዜጋ እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ትግራይን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ዜጋ እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ
ባህርዳር ጥር 21/2013 (ኢዜአ) የትግራይን ክልል መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት መላው ኢትዮጰያውያን ተገቢውን ትብብርና እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ጥሪ አቀረቡ።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ትላንት ምሽት በባህርዳር ከተማ የአማራ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር ሽኝት ላይ እንዳሉት የትግራይ ህዝብ ከመላው ኢትዮጰያውያን ጋር ለዘመናት ለኢትዮጵያ አንድነት ሲታገል የኖረ ነው።
በተለይም የአማራና የትግራይ ህዝብ በማንኛውም መንገድ ሊለያይ የማይችል እርስ በእርስ የተዋለደና በባህል በሃይማኖት የተሳሳረ አንድ ህዝብ ነው።
ይሁን እንጂ በህውሃት የአመራር ዘመን ከመደጋገፍና መተጋገዝ ይልቅ መገፋፋት በርትቶ መቆየቱን ገልጸው “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተገቢ አለመሆኑን ያምናል” ብለዋል።
“የህውሃት ጁንታ መሪዎች በፈጠሩት ችግርም የትግራይ ህዝብ ባላሰበውና ባልገመተው ሁኔታ ከማንም በላይ ለከፋ ችግር ተጋልጧል”ብለዋል።
ጁንታው አሁንም ቢሆን የወሰንና መሰል አጀንዳዎችን በማንሳት ጊዜያዊ አስተዳደሩ እግሩን እንዳይተክልና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖር እየሰራ መሆኑንም ናግረዋል።
ጁንታውን የማስወገድ ዋናው ስራ የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን አሁንም መልሶ የማደራጀትና ፈታኝ የህግ ማስከበር ስራዎች እንዳሉ ዶክተር ሙሉ አብራርተዋል።
“በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን የትግራይን ህዝብ መልሶ ለማደረጀት በሚደረገው ርብርብ ተገቢውን እገዛና ድጋፍ የሚያስፈልግበት ወሳኝ ሰዓት ላይ ነው” በማለት ለዚህም የቀደመ የመተባበርና የመተጋገዝ ባህላችን መሰረት ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ በኋላ በሃይልና በጉልበት እኔ አውቅልሃለሁ የሚባልበት ጊዜው አልፏል “ያሉት ዶክተር ሙሉ በሚገጥሙ ጉዳዮች ዙሪያ በጠረጴዛ ዙሪያ በህግና ስርዓት በውይይት ይፈታል ብለዋል።
የትግራይ መንግስት መልሶ እንዲዋቀር ማገዝ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ናቸው።
ጁንታው በፈጠረው ችግር የትግራይ ህዝብ አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለም ተናግረዋል።
“ለዚህም የክልሉን መንግስት መልሶ በማቋቋም የህዝብ ጥያቄ የሚያስተናግድ ሃይል እንዲኖር ጊዜያዊ አስተዳደሩን በቁርጠኝነት መደገፍ ይገባል”ብለዋል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው “የትግራይ ህዝብ ለበርካታ ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር መስዋትነት የከፈለ ታላቅ ህዝብ ነው”ብለዋል።
“ይሁን እንጂ ለህዝባቸው በማይጨነቁ የራሱ ልጆች ያቀነባበሩት የጦርነት ድግስ ህዝቡን ለችግር ዳርጎታል”ብለዋል።
“በመሆኑም ጦርነት የሰለቸው የትግራይ ህዝብ ከጉያው የወጡ ጠላቶቹን በቃችሁ በማለት በአካባቢው ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ሊሆን ይገባል’ሲሉም ተናግረዋል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ክልሉ ወደ አንፃራዊ ሰላም እስኪመለስ ድረስ በሚችለው አቅም ሁሉ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።