ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የቅርጫት ኳስ ፕሪሜየር ሊግ ውድድር በሀዋሳ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ድሬዳዋ፤ ጥር 21/05/2013  (ኢዜአ) በድሬዳዋ አሰተዳደር ሲካሄድ የቆየው ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የቅርጫት ኳስ ፕሪሜየር ሊግ አንደኛ ዙር ውድድር በሁለቱም ጾታ በሀዋሳ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡

ኮሮናን በመከላከል ከጥር 16/2013ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት በተጠናቀቀው በዚሁ ውድድር ላይ አራት የሴቶች እና አምስት የወንዶች ክለቦች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የውድድሩን ሁሉንም ጨዋታዎች አሸንፎ ስምንት  ነጥብ በማስመዝገብ ሀዋሳ አንደኛ ፣ በሰባት ነጥብ ወልቂጤ ሁለተኛ፣ ድሬዳዋ ደግሞ  በአራት ነጥብ ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

በሴቶች ምድብም  ሀዋሳ ከተማ አንደኛ፣ ወልቂጤ ከተማ  ሁለተኛ እና  አማራ  መንገድና  ህንጻ አማካሪ ሶስተኛ ሆነዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማው ዳንኤል አስፋው ወንዶች እና ሊድያ  ዴቪድ ደግሞ ከሴቶች በከፍተኛ ነጥብ አስቆጣሪነት ኮከብ መሆን ችለዋል፡፡

በውድድሩ ከርቀት   ነጥቦችን በማስመዝገብ የድሬዳዋ ከነማ ተጫዋች አዩብ ኡስማን ኮኮብ ሲሆን በሴቶች ደግሞ የሀዋሳ ከተማዋ ተጫዋች መቅደስ አባተ ሆናለች፡፡

የሁለተኛው ዙር ውድድር ደግሞ በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ  እንደሚካሄድ  የኢትዮጵያ  ቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል፡፡

የፌደሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ኃይሌ በድሬዳዋ  የተደረገው  ውድድር  ደማቅና በጥሩ መስተንግዶ የታጀበ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

አዳዲስና ለብሔራዊ ቡድን ተተኪ ተጨዋቾች የተስተዋሉበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በባህር ዳሩ ጨዋታ እንደ አዲስ ለውድድር የሚመጡ  የቅርጫት ኳስ  ክለቦች  ለነጥባቸው  ማካካሻ እንዲሆን እጥፍ ጨዋታ እንዲጫወቱ ዕድል ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም