የደች ኢንቨስተሮች በአበባና ሆርቲካለቸር ዘርፍን ጨምሮ በሌሎች የግብርና ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የደች ኢንቨስተሮች በአበባና ሆርቲካለቸር ዘርፍን ጨምሮ በሌሎች የግብርና ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ
ጥር 21/2013 (ኢዜአ) የደች ኢንቨስተሮች በአበባና ሆርቲካለቸር ዘርፍን ጨምሮ በሌሎች የግብርና ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።
በኔዘርላንድስ ዘሄግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዲስ አበባ ከሚገኘው የኔዘርላንድስ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በትላንትናው እለት “Ethiopia: Focus on Agricultural Investment” በሚል ርዕስ ዌቢናር ውይይት አካሂዷል።
በወቢናር ውይይቱም ከ50 በላይ የሚሆኑ የዳች ኩባንያዎችና የተለያዩ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አድርገዋል።
አምባሳደር ሚሊዮን ሳሙኤል ለተሳታፊዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት በአሁኑ ወቅት በተለይም በአበባና ሆርቲካለቸር ዘርፍ ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የደች ኢንቨስተሮች የሚገኙ መሆኑን አንስተው፤ ዘርፉ አሁን ካለበት ቁጥር በላይ ኢንቨሰትመንት የመሳብ አቅም ያለው በመሆኑ አቅም ያላቸው የደች ኢንቨስተሮች በዚህም ሆነ በሌሎች የግብርና ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዌቢና ውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ኢንቨትመንት ማስፋፋት እና ቴክኖሎጂ ትራንሰፈር ዳይሬክቶሬት ጄነራል አምባሳደር አባቢ ደምሴ ዌቢናሩ በግብርና ዘርፍ ላይ ማተኮሩ ጊዜውን የጠበቀና ለሀገሪቱም በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በገበርናው መስክ ላይ ያለውን የሀገራችን አቅምና የገበያ ዕድሎች በመገንዘብ ከኔዘርላንድስ ጋር በይበልጥ ለመተሳሰር ዌቢናሩ መልካም አጋጠሚ የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል ።
የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት ገለጻ የግል ዘርፉን በግብርና ላይ በስፋት ተሳታፊ ለማድረግ ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ከፍተኛ ሪፎርም በማደረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዝናብና በመስኖ በመጠቀም ለግብርና ጥቅም ላይ እያዋለ ያለው መሬት መልማት ከሚችለው 1/6ኛ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ምርታማነትን ለመጨመር የግሉን ሴክተር በስፋት ማካተት እንደሚገባ በመረዳት ከፖሊሲ ጀምሮ የተለያዩ አሰራሮች እየተሻሻሉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ከኢንቨሰትመንት ኮሚሽንን የተሳተፉት የኢንስትመንት ፕሮሞሽን በላሙያ ወይዘሪት ረድኤት ይሕአለም በበኩላቸው ሀገራቱ በግብረና ዘርፍ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርጓትን ምቹ ዕድሎች ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በተለይም በሰሊጥ፣ በወተትና ወተት ተዋጽኦ(dairy)፣ የእንስሳት መኖ (animal feed) እና የዶሮ ልማት (poultry) ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት መሆኗንና ለዚህ ዘርፍ የተመቻቹ ማበረታቻዎች ላይ ማብራራርያ ሰጥተዋል፡፡
በዌቢናሩ ሁለተኛ ዙር ላይ በአዲስ አበባ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ የግብርና ካውንስለር የሆኑት Mr. Meeuwes Brower ባቀረቡት ገለጻ በአሁኑ ወቅት ከ85 በላይ የሚሆኑ የደች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ መሆኑን በማንሳት ከዚህም 80 በመቶ የሚሆኑት በግብርና ላይ ተሰማሩ መሆናቸውንና ኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ የወጪ ምርት ተደራሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በኔዘርላንድስ ትኩረት የሚሰጥባቸውን የግብርና መስኮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የ Wageningen University and Research center, የዓለም ዐቀፍ ትብብር የአፍሪካ ማኔጀር የሆኑት Ms Jennie van der Mheen ባቀረቡት ገለጻ ዩንቨርስቲያቸው ከሚያድረገው የጥናት እና ምርምር ስረዎች አንጻር በዘርፉ ላይ ያለውን የሀገራችንን አቅም በማንሳት በዘርፉ ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለማገዝ የጥናት ተቋሙ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
Senselet Food Processing, Alema Koudijs/ Royal De Heus, Afriflora/ Sher የተሰኙ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ተሰማርተው የሚገኙ ሶስት የደች ድርጅቶች ተወካዮችም የልምድ ልውውጥ ያደረጉ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ በነበረው ፓናል ውይይት ሀገር ቤት የሚገኙ ኢንቨስተሮች ሚያጋጥማቸውን ችግሮች መፍታት ተጨማሪ ኢንቨስተሮች ለማሳብ ቁልፍ ሚና የሚኖረው በመሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቋሚ ግንኙነቶችን በመፍጠር ቅሬታቸውን መፍታት እንደሚገባ መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።