በቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የፌዴራል ማረሚያና የሙገር ጨዋታ ተቋረጠ - ኢዜአ አማርኛ
በቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የፌዴራል ማረሚያና የሙገር ጨዋታ ተቋረጠ
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 በዘንድሮው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ፌዴራል ማረሚያና ሙገር ሲሚንቶ ትናንት ያደረጉት ጨዋታ ሳያልቅ ተቋርጧል። በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ "በዳኞች ውሳኔ ደስተኛ ያልነበሩት የፌዴራል ማረሚያ አሰልጣኝ ቡድናቸው ጨዋታውን አቋርጦ እንዲወጣ ማድረጋቸውን" የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የሶስት ጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች ተጠናቀው አራተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሙገር 20 ለ 12 እየመራ ጨዋታው መቋረጡን ተናግረዋል። ሙገር ሲሚንቶ ጨዋታውን ሁለት ለአንድ እየመራ ነበር። የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ነገ ስብሰባ እንደሚያደርግና የጨዋታው ኮሚሽነር በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ በመመስረት ውሳኔ እንደሚያስተላልፍም ነው አቶ ተክሉ ያስረዱት። ትናንት ክልል ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ ጣና ባህርዳር ወላይታ ድቻን በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሶስት ለሁለት በሆነ ውጤት አሸንፏል። በበጀት ችግር ምክንያት የተወሰኑ ጨዋታዎች ይራዘምልኝ ብሎ ጥያቄ ያቀረበው ጣናባህርዳር ከፌዴሬሽኑ ተቀባይነት በማግኘቱ ያለፉትን ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አለማድረጉን አስታውሰዋል። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሰባት ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ነው። በተያያዘም የ2010 ዓ.ም የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሶስት ለዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፏል። በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አራት ቡድኖች ብቻ ናቸው የሚሳተፉት። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ወንዶችና ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።