ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በእንግሊዝ የፓርላማ አባል የተመራ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20/2013 ( ኢዜአ) በእንግሊዝ የፓርላማ አባል የተመራ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አደነቀ።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በእንግሊዝ የፓርላማ አባል የተመራ የልዑካን ቡድንን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት እቅድ ውስጥ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ከዋንኛ ምሰሶዎች መካከል አንዱ እንደሆነም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ የደን ልማት ውጤት እያስገኘ እንደሆነም አቶ አህመድ ገልፀዋል፡፡

የወቅቱ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፕሬዝዳንት አሎክ ሻርማ ለአየር ንብረት አጀንዳ ስኬታማነት የካርቦን ልቀትን መቀነስ፣ የደን ጭፍጨፋን መከላከል ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ ዓለም አቀፍ ትብብርን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑንም አፅንዖት ሰጥተዋል ፡፡

የደን መጨፍጨፍን በመቀነስ እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለማሳካት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት አበረታተው ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት መሆኗንም ጠቅሰዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ አገራት የመቋቋም አቅም መገንባት እንዲችሉ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል ፡፡

እ.ኤ.አ ኖቬምበር 2021  በግላስጎው የሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ የእንግሊዝን ጥረት ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ ገልፀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም