ቀጥታ፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ኢትዮጵያዊያንን ለመታደግ የዜጎች ፈንድና የኢትዮጵያ የሕግ ጠበቃ እንዲቋቋም ዲፕሎማቶች ጠየቁ

ጥር 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ችግር የሚያጋጥማቸውን ኢትዮጵያዊያን ለመታደግ በመንግስት የዜጎች ፈንድና የኢትዮጵያ የሕግ ጠበቃ እንዲቋቋም ዲፕሎማቶች ጠየቁ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝተው የተቋሙን ተልዕኮ የሚያዘምኑ ስራዎችና የሕጻናት ማቆያውን ጎብኝተዋል።

ኮቪድ-19ን ተከትሎ የተደራጀውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል የተመለከቱ ሲሆን እግረ መንገዳቸውን በእስያ አገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ቆንስላ ጄኔራሎች ጋር በዌቢናር ተወያይተዋል።

አምባሳደሮቹ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ስላነጋገሯቸው አመስግነው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቢኖርም በዚህ መንገድ እየተወያዩ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በጋራ ሲከውኑ መቆየታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ከአምባሳደሮቹ ሃሳቦች መካከል በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለችግር እንደሚጋለጡ ያነሱበት አንዱ ነው።

በዚህም በተለያዩ ጉዳዮች ሕግ ፊት ሲቀርቡ ገንዘብ ከፍለው ከእስር መለቀቅ የሚችሉበት ዕድል እያለ አቅም በማጣታቸው ለበርካታ ዓመታት በእስር እንደሚማቅቁ ለአብነት ጠቅሰዋል።

እንዲህ አይነቶቹን ችግሮች ለመፍታት 'የዜጎች ፈንድ ቢቋቋም' የሚል ሃሳብ ከአምባሳደሮቹ ተነስቷል።

ኢትዮጵያን ወክሎ የሚከራከር የሕግ ጠበቃ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ውስጥ ቢመደብ የሚልም ሃሳብም ከዲፕሎማቶቹ ተነስቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አምባሳደሮቹ ኢትዮጵያን ወክለው በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዲፕሎማሲ መስክ እያከናወኑ ስላለው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

መንግስት ለተልዕኳቸው ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም አረጋግጠዋል።

ዲፕሎማቶቹ ባሉባቸው አገሮች የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት በዚያ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላትና ተማሪዎች ጋር በመተባበር እንዲሰሩም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም