በሀገራዊ በወቅታዊ ጉዳዮች በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል ...አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ በወቅታዊ ጉዳዮች በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል ...አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በወቅታዊ ጉዳዮች የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ረገድ ስኬታማ ስራዎች ማከናወኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የተጠሪ ተቋማት ተወካዮች ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመስሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማቱ ዕቅድ አፈጻፀም ላይ ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ ባለፉት ስድስት ወራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ያልተጠበቀው የሕግ ማስከበር ባለበት በመደበኛና በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውጤታማ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያዊ ክንውኖችን ማሳካቱን አንስተዋል።
በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያ ሕግ የማስከበር ተልዕኮን ተከትሎ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይጠይቅ እንደነበረና በርካታ ወገኖችም በጉዳዩ እጃቸውን ለማስገባት ፍላጎት እንደነበራቸው ገልጸዋል።
የሕግ ማስከበር ተግባር ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንደሚያመራና ውስብስብ እንደሆነ የገመቱ አካላት እጃቸውን ለማስገባት ቢፈልጉም ሂደቱ በአጭር ጊዜ በመጠናቀቁ እንዳልተሳካላቸው አንስተዋል።
የሕግ ማስከበር ስራው በአጭር ጊዜ ቢጠናቀቅም በመልሶ ማቋቋምና በሠብዓዊ ድጋፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማጋነን በጅምላ ፍረጃ የኢትዮጵያን ገፅታ የሚያጠለሹ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ገፅታ ከሕዳሴ ግድብና ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ ፍላጎት ያላቸው ሃይላት ጉዳዩን ሚዛን ባልጠበቀ አግባብ ሲያራግቡት መቆየታቸውንም አውስተዋል።
ስለ ሕግ ማስከበሩ ለአገራት፣ ለአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት በማስረዳት ውጤታማ የፖለቲካ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች መከናወናቸውን በመግለጽ፤ የአገሪቷን ገጽታ የመገንባትና መሬት ላይ ስላለው እውነታ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ቢከናወኑም፤ ቀደም ሲል የነበረውን የተዛባ ትርክትና ጅምላ ወቀሳ የማስተካከል ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።
በዓለም አገራት በሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላ የኢትዮጵያ ተወካይ ዲፕሎማቶችም ከሚገኙበት አገር ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ኢትዮጵያ የሚነገረውን በመገምገም ስራዎችን በቅንጅት እንዲሰሩ ሲደረግ መቆየቱን አብራርተዋል።
ሁሉም ዲፕሎማት በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም ማኅበረሰብ እንዲያሳውቅ የማድረግ ስራዎችም ተሰርተዋል ነው ያሉት።
የዳያስፖራው ማኅበረሰብም ከኢትዮጵያ በመወገን ሲሰራ እንደነበር ገልጸው፤ ዳያስፖራው የሚያንቀሳቅሰው ካለ ብዙ መስራት እንደሚቻል ያሳየ እንደሆነም ገልጸዋል።
"የአገር ገጽታና ጥቅም የሚጠበቀው በመንግስት ዲፕሎማቶች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአገሩ ጉዳይ ዲፕሎማት ሆኖ ሲከራከር ነው"ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ለውጡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ ሲሰሩ የነበሩ ወገኖች እንደነበሩ ጠቅሰው የአፍሪካ ኅብረትን አብነት አንስተወል።
ኢትዮጵያ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ መስክ ውጤታማ ለመሆን ስትራቴጂክ ወዳጆቿን ለማብዛት በፖሊሲና በዕቅድ አስደግፋ እየሰራች መሆኗንም ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷ ከአባል አገራቱ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎች ከቦታ ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን መድፈንና የደህነንት ዋስትና ተግዳሮቶችን ማሻሻል እንደሚገባም ገልክጸው፤ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አውስተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮና ሌሎች አባላትም አቶ ደመቀ ቀድሞ አገራዊ ለውጡ እንዲመጣ፤ አሁንም በድርብ ሃላፊነት አገሪቷ የገጠማትን ፈተና እንደትወጣ እየሰሩት ላለው ስራ አመስግነዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በየወቅቱ የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ሲከታተል መቆየቱን የገለፁት ዶክተር ነገሪ፤ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
በተለይም አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የአገሪቷ መሪዎች ሕግ የማስከበር ሂደቱን በተመለከተ በተለያዩ አገራት በመገኘት ያከናወኑት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ትልቅ ውጤት ማስገኘቱን አንስተዋል።
በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶች ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኮሙኒቲ በተለይም በተለያዩ አገራት ለትምህርት ከተላኩ ተማሪዎች ጋር በመቀናጀት የአገር ገጽታ ግንባታ ላይ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያጠለሹ የውጭ ሚዲያዎችን በመከተታል ትክክለኛውን መረጃ መስጠት እንደሚገባም ነው ዶክተር ነገሪ የተናገሩት።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም መከፋፈልና ልዩነትን በመተው በአገራዊ ጥቅሞች ላይ በአዎንታዊ መልኩ መስራት አለባቸው ብለዋል።