የግንባታ ፍቃድ እና ተያያዥ አገልግሎቶች በኦንላይን መደረጉ ለተገልጋዩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የግንባታ ፍቃድ እና ተያያዥ አገልግሎቶች በኦንላይን መደረጉ ለተገልጋዩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል
ጥር 20/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቢዝነስ ፖርታል የሚሰጣቸው አገልግሎቶች የግንባታ ፍቃድ እና ተያያዥ አገልግሎቶቹን በኦንላይን ማድረጉ ለተገልጋዩ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገለጸ።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የኢትዮጵያን የንግድ ስራ ቅልጥፍና ማሻሻያ አስፈላጊ የሆነውን የኢትዮጵያ ቢዝነስ ፖርታል (www.business.gov.et) አልምቶ ወደስራ ማስገባቱ ይታወቃል፡፡
የንግድ አሰራርን ቅልጥፍና ለማሻሻል ታሳቢ በማድረግ የለማው የኢትዮጵያ ቢዝነስ ፖርታል የግንባታ ፍቃድ አሰራርን ለማዘመን እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ተጎብኝቷል።
ፖርታሉ በርካታ የዲጂታል አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው፡፡
ፖርታሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ የአዲስ አበባ አስተዳደር የግንባታ አገልግሎት ይገኝበታል፡፡
አገልግሎቱ የግንባታ ፍቃድ፣ የግንባታ ማሻሻያ ፍቃድ፣ ማራዘሚያ እና የፕላን ስምምነት በኦንላይን አገልግሎት ለመስጠት በማስቻል አገልግሎቱ ጊዜንና ጉልበትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በጉብኝቱ የሚኒስቴሩ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የመሰረተ ልማት ቅንጅት እና የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ህላዊ ሰውነት “አገልግሎቱ የግንባታ ፍቃድ እና ተያያዥ አገልግሎቶቹን በኦንላይን ማድረጉ ለተገልጋዩ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር የአሰራር ግልጽነት እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል ለመፍጠር ያግዛል” ብለዋል፡፡
የዲጂታል አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች ለማላመድ የማበረታቻ አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ የኢትዮጲያ ቢዝነስ ፖርታል የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ አገልግሎታቸውን በፖርታሉ በኩል ተደራሽ ያደረጉ ተቋማት በትብብር እና በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
“የአዲስ አበባ ከተማ የመሰረተ ልማት ቅንጅት እና የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ኤጀንሲ ያሳየው ተነሳሽነት ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው” ብለዋል፡፡
በቀጣይም አገልግሎቱን እስከ ክፍለ-ከተሞች ለማውረድ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።