አሜሪካ በኢትዮጵያ በተለያዩ መክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች 170 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ በኢትዮጵያ በተለያዩ መክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች 170 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች
አዲስ አበባ ሐምሌ 17/2010 አሜሪካ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ የሚውል 170 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች። እርዳታው በተፈጥሮ አደጋና ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ዜጎች እንደሚውል በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) የኢትዮጵያ ልዑክ ዳይሬክተር ሌስሊ ሪድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አሜሪካ ኢትዮጵያን የመደገፍ የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት አላት። ሆኖም በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በጊዜያዊ መጠለያ ማቆየት ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆንና መንግስት ዜጎቹ ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ተግባር ላይ ይበልጥ ማተኮር እንዳለበት ተናግረዋል። የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች አስቸኳይ ፍላጎቶችን የሚያሟላ እንደሆነና ጤንነታቸው ተጠብቆ ዜጎች ወደ መኖሪያቸው በሰላም እንዲመለሱ በማድረግ ቀድሞ የነበራቸውን ህይወት ዳግም እንዲጀምሩ የሚያግዝ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የተፈናቀሉት ዜጎች ለመፈናቀላቸው ዋንኛ መንስኤ የሆኑ ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክርል ሬይነር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጋር በመተባበር እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙና ሌሎች ግጭቶች እንዳይነሱ በመከላከል ረገድ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ከኢትዮጵያ አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና ለብዝሃነት ክብር የመስጠት እሴቶች ጋር እንደማይሄዱ ተናግረዋል። ኢትዮጵያውን በአገራቸው እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ ስራዎች ከግብ እንዲደርሱና ውጤታማ እንዲሆኑ መስራት እንዳላባቸውና ግጭትና ማግለል በለውጡ ስራ ውስጥ ቦታ እንደሌለው አስገንዝበዋል። አሜሪካ ዛሬ ይፋ ያደረገችው በኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የ170 ሚሊዮን ዶላር ሰብአዊ እርዳታ አሜሪካ ከህዳር ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለኢትዮጵያ በሰብአዊ እርዳታ ያደረገቸውን ድጋፍ ከ802 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያደርሰው ኤምባሲው አስታውቋል። በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ከብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።