ከሮቤ-ጋሰራ-ጊኒር የሚገነባው የአስፓልት መነገድ ሥራ መጓተት ቅሬታ ፈጠረ - ኢዜአ አማርኛ
ከሮቤ-ጋሰራ-ጊኒር የሚገነባው የአስፓልት መነገድ ሥራ መጓተት ቅሬታ ፈጠረ
ጎባ ፤ጥር 19/2013 (ኢዜአ)፡-ከሮቤ- ጋሰራ-ጊኒር የሚገነባው 121 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ መጓተቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የምስራቅ ባሌ አካባቢ ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ገለጹ፡፡
በአሽከርካሪነት የተሰማሩት አቶ መስፍን ከበደ እንዳሉት የመንገዱ ገንባታ ከመጓተቱ ባለፈ ተቋራጩ ተለዋጭ መስመር በአግባቡ ባለመስራቱ የተቆፋፈረው መንገድ ተሽከርካሪያቸው በተደጋጋሚ ለብልሽት በመጋለጥ ተቸግረዋል።
ተለዋጭ መንገዱ በአግባቡ ባለመሰራቱ ከዚህ በፊት ሁለት ሰዓት ያስኬድ የነበረው የጊኒር- ሮቤ መንገድ እስከ አምስት ሰዓት እንደሚፈጅባቸው ተናግረዋል፡፡
በግንባታ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሉኡል መንግስቱ በበኩላቸው የመንገዱ ግንባታ ከመዘግየቱም በላይ የጥራት ችግር እንዳለበት አስረድተዋል።
በዚህ መልኩ ተሰርቶ ቢጠናቀቅ ጉዳት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የመንገዱ ግንባታ ሥራው በመጓተቱ በዕለት ተለት ሥራቸው ላይ እንቅፋት በመሆን ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ መሐመድ አልይ ናቸው።
መንገዱ ሲጀመር በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ቢነገራቸውም አሁን ላይ ከአምስት ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን ገልጸዋል፡፡
የጊኒር ከተማ ነዋሪ አቶ ጣህር አብደላ አካባቢያቸው ትርፍ አምራች ቢሆንም ምርታቸውን ወደ ገበያ አቅርበው የተሻለ ገበያ ለማግኘት በመንገድ ችግር ተወስነው በደላላ እየተነጠቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"ተቋራጩ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም ማሽነሪ ነቅሎ ከአካባቢው በማውጣቱ በውሉ መሰረት መንገዱን ገንብቶ ለአገልግሎት ያበቃል ተብሎ ስለማይታሰብ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እልባት ሊሰጡት ይገባል" ብለዋል፡፡
የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም በበኩላቸው ህብረተሰቡ ስለአስፓልት መንገድ ግንባታ ሂደት ላይ ሚያነሳው ቅሬታ ትክክልና አግባብነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ በየደረጃው ለሚገኙ የሚመለከታቸው የክልልና ፌዴራል መንግስት አካላት ሪፖርት በማድረግ በመፍትሄው ላይ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የመንገዱን ግንባታ በተቋራጭነት የወሰደው የአፍሮ ጽዮን የመንገድ ግንባታ ኮንስትራክሽን ተወካይ ስለ ጉዳዩ በስልክ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ቢሞክርም ማግኘት አልተቻለም።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣና ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ሰሞኑን በባሌና ምስራቅ ባሌ ዞኖች ውስጥ እየተገነቡ የሚገኙ የአስፓልት መንገዶችን በተመለከቱበት ወቅት እንዳሉት ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳበቸው የሮቤ-ጋሰራ-ጊኒር የመንገድ በተፈለገው ፍጥነትና ጥራት ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ድጋፍና ክትትል ይደረጋል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብና በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ለመንገድ ግንባታው ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የባሌንና ምስራቅ ባሌ ዞኖች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኮሪደር በመሆናቸው አካባቢውን ከመሃል ሀገር፣አጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር በአስፓልት መንገድ ለማስተሳሰር እየተሰራ ያለውን መንገድ ጠቅሰዋል።
ኢንጂነር ሀብታሙ የጠቀሱት የደሎ ሰብሮ-ድሬ ሼህ ሁሴን፣ጎባ-ደሎ መና-ነጌሌ፣ጊኒር -ጎዴ፣ከሮቤ-ጎሮ የሚባሉ አዳዲስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ነው፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የመንገድ ፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም በተመለከተ ሰሞኑን ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የአስተዳደር አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡