ቀጥታ፡

በጁባ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ለአገራቱ እርቅ ድጋፋቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ ሀምሌ 17/2010 በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ለሁለቱ አገራት እርቅ ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በጁባ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን በሁለቱ አገራት መካከል የወረደውን እርቅ በመደገፍ ከትናንት በስቲያ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍስሃ ሻውል በሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ እርምጃዎች አድንቀዋል። በዚህም በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ የሁለቱ አገራት ዜጎች አሁን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ሕብረቱን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል። በደቡብ ሱዳን የኤርትራ አምባሳደር ዮሐንስ ተክለሚካኤል በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል የወረደው ዕርቅ መሪዎቹን የሚያስመስግንና ለአካባቢው አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል። በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የሠላም እና የወዳጅነት ስምምነት ኤርትራዊያንን ያስደሰተ መሆኑንም አምባሳደር ዮሐንስ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም