የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በእቅድ ማስኬድ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በእቅድ ማስኬድ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 19/2013 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በእቅድ ማስኬድ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የወጣቶች በጎ ፍቃድ ማስተባባሪያ ቢሮና የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በእቅድ ማስኬድ የሚያስችል የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፍኖተ ካርታው ከዚህ ዓመት ጀምሮ እስከ 2022 ዓ.ም ለቀጣይ 10 ዓመታት እንደሚቆይ ተገልጿል።
በስምምነቱ ወቅት የከተማዋ የወጣቶች በጎ ፍቃድ ማስተባባሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ እንደገለጹት "የበጎ ፍቃድ ስራ ወደ ማህበረሰቡ በደንብ ዘልቆ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
የፍኖተ ካርታ ዝግጅቱ ዋነኛ ዓላማው የበጎ ፍቃደኝነት ስራው የት ደርሷል? እንዴትስ መቀጠል አለበት? የሚለውን ለመመለስ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም ከተቋሙ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ጋር በማካተት የበጎ ፍቃድ ስራን የት እናድርሰው የሚለውን ጥያቄ ለመመለሰ ያስችላል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሆኑ ይህንኑ በአሰራርና በህግ ለመደገፍ ፍኖተ ካርታው ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ገልጸዋል ።
ከኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት አቶ ዘመኑ በጋሻው በበኩላቸው ፍኖተ ካርታው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ ይተገበራል ብለዋል ።
ፍኖተ ካርታው አሁን ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት በቀጣይ 10 ዓመታት ይተገበራል ብለዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በእቅድ ለመምራት ለኢንስቲትዩቱ በጋራ የእንስራ ጥያቄ ሲቀርብለት የመጀመሪያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባር የሚያከናውኑ ድርጅቶች የሚሰሩትን ስራ በእቅድ ለመምራት ፍኖተ ካርታው ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ተገልጿል።