በአፋር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የ71 ባለሀብቶች ፍቃድ ተሰረዘ

ሰመራ፤ጥር 19/2013(ኢዜአ) በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የ71 ባለሀብቶችን ፍቃድ መሰረዙን የአፋር ክልል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

በክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ የመከረ መድረክ ትላንት በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።

በኮሚሽኑ የኢንቨስትመንት ማበረታቻና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እድሪስ እስማኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ባለሀብቶቹ ከአራት አመት በፊት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ ቢወስዱም እስካሁን ወደ ስራ ባለመግባታቸው ፍቃዳቸው ተሰርዟል።

ባለሀብቶቹ በክልሉ በቂልበቲ-ረሱ ዞን በአበአላ ከተማ አስተዳደር ለሆቴል ግንባታ የተረከቡት ከ67 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን አስታውቀዋል።

በክልሉ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ካለው አስተማማኝ ሰላም በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ፍቃድ አሰጣጥ ጨምሮ ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ በመሆኑ በዘርፉ የሚሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል ።

በአመታቱ 116 ባለሃብቶች በእርሻ፣ በእንስሳት ሃብትና በማዕድን ልማት ፍቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
 
ከባለሀብቶቹ ውስጥ 48ቱ ወደ ስራ የገቡና 36ቱ ደግሞ በዝግጅት ምዕራፍ ላይ ያሉ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ቀሪዎቹ ግንባታ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ባጠቃላይ ባለሀብቶቹ በተሰማሩባቸው መስኮች  ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል ተፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም