የፕሪሚየር ሊግ ጥሎ ማለፍ ውድድር ካፍ ካስቀመጠው ጊዜ ገደብ በፊት ይጠናቀቃል-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊግ ጥሎ ማለፍ ውድድር ካፍ ካስቀመጠው ጊዜ ገደብ በፊት ይጠናቀቃል-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ ሀምሌ 17/2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ የ2010 ዓ.ም ውድድርን ካፍ ካስቀመጠው ጊዜ ገደብ ቀድሞ እንደሚያጠናቅቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ካፍ) አገራት በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ውድድር የሚሳተፉ ክለቦችን ዝርዝር ከጥቅምት 5 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት እንዲያሳውቁ የጊዜ ገደብ ማውጣቱ ይታወሳል። ኢትዮጵያም በዚህ አህጉር አቀፍ ውድድር ላይ የሚወክላትን ክለብ ለማሳወቅ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድሮችን ከሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም አንስቶ እያካሄደች ነው። ይሁንና በዝናብ ምክንያት ጨዋታዎችን ማካሄድ ባለመቻሉ ቀጣይ የሐዋሳ ከተማና ሲዳማ ቡና አሸናፊ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ፤ እንዲሁም የግማሽ ፍጻሜ፣ የፍጻሜና የደረጃ ጨዋታዎችን ከመስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንዲካሄዱ ተወስኗል። ጨዋታዎቹ የሚካሄዱባቸውን ቀናትና ቦታዎች በቀጣይ ጊዜያት እንደሚያሳውቅም ፌደሬሽኑ ገልጿል። በጥሎ ማለፉ ለዋንጫ ለማለፍ መከላከያ ከኢትዮጵያ ቡና የሚጫወቱ ሲሆን በሩብ ፍጻሜው አንድ ጨዋታ ሲዳማ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚጫወቱ ሲሆን የሁለቱ አሸናፊ ከፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ጅማ አባጅፋር ጋር በግማሽ ፍጻሜው ይጫወታል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በወጣለት መርሃ ግብር መሰረት ሳይጠናቀቅ እየቀረ ወደ ቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ሲራዘም ይስተዋላል። ይህ መሆኑ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ላይ ተጽእኖ ሲያሳድርም ይታያል። በአፍሪካ አገራት በሚደረጉ የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ክለቦች በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳታፋሉ። ካፍ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጥሎ ማለፉን ውድድር አጠናቆ ለካፍ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈውን ክለብ ከጥቅምት 5 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት ያሳውቃል ተብሏል። የዘንድሮው ዓመት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ 16 ቡድኖች በአራት ምድብ ተከፍለው ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ እየተፋለሙ ሲሆን አጠቃላይ ውድድሩ ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል። የ2011 ዓመት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጥር ወር 2011 ዓ.ም ይጀመራል። በዘንድሮው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው ወላይታ ድቻ የዛንዚባሩን ዚማሞቶና የግብጹን አንጋፋ ክለብ ዛማሌክ አሸንፎ 32 ውስጥ በመግባት አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። ይኸው ክለብ ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር ተጫውቶ በድምር ውጤት 2 ለ 1 ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበቱ የሚታወስ ነው።