ቀጥታ፡

በምርት ገበያ በኩል ለሚከናወኑ ግብይቶች ክፍያ የሚያስፈፅሙ ባንኮች ቁጥር አደገ

አዲስ አበባ 17/2010 በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ለሚከናወኑ ግብይቶች ክፍያ የሚያስፈፅሙ ባንኮች ቁጥር 13 ደረሰ። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ለደቡብ ግሎባል ባንክ የምርት ገበያን ግብይት ክፍያ እንዲያስፈፅም የሚያስችል ዕውቅና ዛሬ ሰጥቷል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኡሌሮ ኦፒየው እንደተናገሩት ፤ ምርት ገበያው ከ10 ዓመት በፊት ስራ ሲጀመር በባለስልጣኑ ዕውቅና ተሰጥቷቸው ግብይቶችን ሲያስፈጽሙ የነበሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ዳሽን ባንክ ብቻ ነበሩ። የባንኮቹ ቁጥር በየዓመቱ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ደቡብ ግሎባል ባንክን ጨምሮ ቁጥራቸው 13 ደርሷል። ለግብይት ሂደቱ ተፈላጊውን መስፈርት በማሟላት ክፍያ የሚያከናውኑ ባንኮች ቁጥር ማደግ ዘመናዊ የክፍያ ማስፈፀም አቅምን በማስፋትና ሂደቱንም የተቀላጠፈ በማድረግ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲጎለብት የሚያግዝ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። ዕውቅና የተሰጣቸው የክፍያ መፈጸሚያ ባንኮች በአባላትና በደንበኞች የባንክ ሂሳብ ውስጥ ገንዘብ የሚሰባሰብበትን ሁኔታ ከማመቻቸት ባሻገር በባለስልጣኑ የክፍያ መፈጸሚያ ተቋም በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረትም ከግብይት በኋላ ገንዘብ ያዘዋውራሉ። ወቅታዊ የአባላትና የደንበኞች የባንክ ሂሳብን የተመለከተ መረጃ መለዋወጥም ሌላኛው የባንኮቹ ተግባር መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል። የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አዲሱ ሃባ በበኩላቸው፤ ባንኩ የምርት ገበያው የክፍያ ፈጻሚ ለመሆን የቻለው ተፈላጊውን መስፈርት ለማሟላት የሚያስችለውን ሂደት ካለፈ በኋላ መሆኑን ገልፀዋል። በምርት ገበያው ግብይት ተካሂዶባቸው ክፍያ እንዲያስፈፅሙ ዕውቅና በተሰጣቸው ባንኮች አማካኝነት የተከናወነው የምርት ሽያጭ መጠን በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ከ33 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም