ቀጥታ፡

"ቀጣይ ግባችን በቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ መሳተፍ ነው" የቦክስ ተወዳዳሪዎች

አዲስ  አበባ ግንቦት 6/2010 "ቀጣይ ግባችን ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ መሳተፍ ነው"  የአፍሪካ የወጣቶች ቦክስ ውድድር ተሳታፊዎች። በሞሮኮ ካዛብላንካ ከሚያዚያ 27 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው የአፍሪካ የወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ሁለት ወርቅና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኘው የልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል። የልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። በውድድሩ በሴቶች በኩል ኢትዮጵያን በብቸኝነት የወከለችው ሀና ደረጀ በ48 ኪሎ ግራም ለአገሯ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች። በተመሳሳይ በወንዶች አራት አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን ከአራቱ ወንድ ተሳታፊዎች መካከል በ49 ኪሎግራም የተካፈለው እንዳሻው አላዩ የወርቅ ሜዳሊያን አግኝቷል ። በዚህ ውድድር ለአገሩ የነሃስ ሜዳሊያ ያመጣው ደግሞ በ64 ኪሎ ግራም የተወዳዳረው ተመስገን ምትኩ ነውበ48 ኪሎ ግራም የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘቸው የ17 ዓመት ታዳጊ ሀና ደረጀ በግማሽ ፍጻሜው ከአልጄሪያ፤ በፍጻሜው ከቱኒዚያ ተጋጣሚዎቹ ጋር ያደረገችው ፉክክር እጅግ ፈታኝና ተመጣጣኝ እንደነበር ገልጻለች። ከአሰልጣኝ ከድር ከማል ባገኘችው ታክቲክና ምክር በመታገዝ፤ እንዲሁም የግል አቅሟን በመጠቀም አሸናፊ መሆኗን ተናግራለች። ኢትዮጵያን ወክሎ መወዳደር ትልቅና ከባድ አደራ መሆኑን፣ አደራውን ተቀብላ በማሸነፏ በጣም ደስተኛ እንደሆነችና ድሉ ለቀጣይ የቦክስ ውድድር ቆይታዋ ብርታት መሆኑን ገልጻለች። "በቀጣይ የእኔ ትልቁ ግብ በቦክስ ስፖርት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ መሳተፍ ነው" ነው ያለችው ሀና ለዚህም በጥቅምት 2010 ዓ.ም በቦነስ አይረስ በሚካሄደው የዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ ማጣሪያ ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት እንደምታደርግ ገልጻለች። በ49 ኪሎ ግራም ተካፍሎ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው እንዳሻው አላዩ "በአዲስ አበባ ለውድድሩ ያደረግነው ጠንካራ ዝግጅት በሞሮኮ ውድድር ላይ ውጤታማ እንድንሆን አድርጎናል" ብሏል። ከተወዳዳሪዎች ጋር የነበረው ፉክክር ከባድና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም የነበረን ጠንካራ የቡድን መንፈስ ውጤታማ እንዲኑ ማድረጉን ተናግሯል። እንዳሻው ባለው ወቅታዊ ብቃት በቶኪዮ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ለመሳተፍ የሚደረገውን ማጣሪያ በማለፍ አገሩን ወክሎ እንደሚሳተፍ ያለውን እርግጠኝነት ገልጿል። በ64 ኪሎ ግራም የነሐስ ሜዳሊያ ያመጣው ተመስገን ምትኩ በተወሰኑ ስህተቶች ምክንያት በሞሮኮ አቻው ተሸንፎ ወደ ፍጻሜ ማለፍ እንዳልቻለ ይናገራል። በኦሎምፒክ ማጣሪያው መሳተፍ ባይችልም በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም በሀንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት በሚካሄደው የዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ለአገሩ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚጥር ገልጿል። በኢትዮጵያ እጅጉን ተዳክሞ የሚገኘውን የቦክስ ስፖርት ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብሏል። የቦክስ ቡድኑ አሰልጣኝ ከማል ከድር ውድድሩ ከጠበቅነው በላይ በጣም ከባድና ፈታኝ ውድድር ነበር በማለት ለኦለምፒክ ማጣሪያ ለማለፍ በመሆኑም ሁሉም አገራት ጠንካራ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቋል። አንድ ወርቅ፣ አንድ ብርና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበርና ሁለት ወርቅ በማምጣት የተሻለ ስኬት ማስመዝገብ እንደተቻለ ተናግሯል። ከሞሮኮው ውድድር በታክቲክ፣ በዳኝነት ህጎችና በስልጠና ላይ ያሉብንን ክፍቶች ማየት እንደታቻለና ለቀጣይ ውድድሮች ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚሰራም ነው አሰልጣኝ ከድር የገለጸው። የኢትዮጵያ የቦክስ ቡድን በሞሮኮው ባሳየው ስፖርታዊ ጨዋነትና የቡድን መንፈስ ከሚዲያዎችና ከሌሎች አካላት አድናቆት እንደተቸረውም አንስቷል። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን በውድድሩ ላይ የተመዘገበው ውጤት በኢትዮጵያ የተዳከመውን ስፖርት ለማነቃቃትና ቀድሞ ወደ ነበረበት ዝናው ለመመለስ ጥርጊያ መንገድ የሚከፍት ነው ብለዋል። በተጨማሪም ውጤቱ በቦክስ ስፖርት ላይ ይበልጥ ከተሰራ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ነው የተናገሩት። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በቀለ ተወዳዳሪዎች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረጋቸው አመስግነው ለቀጣይ ስኬት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈጻሚ አባል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የቦክስ ተወዳዳሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት አገርን የሚያኮራና ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ ስፖርቶች ውጤታማ መሆን የምትችልበት እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብላለች። በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኙት ሀና ደረጀና እንዳሻው አላዩ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም በአርጀንቲና ርዕሰ መዲና ቦነስ አይረስ ቡዳፔስት በሚካሄደው የዓለም ወጣቶች የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ። በተጨማሪም ሀና ደረጀ፣እንዳሻው አላዩና የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘው ተመስገን ምትኩ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም በሀንጋሪ ቡዳፔስት በሚካሄደው የዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ላይ ተካፋይ ይሆናሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም