ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር የጋራ ኮሚሽን ሊያቋቁሙ ነው

39

ጥር 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር የጋራ ኮሚሽን ሊያቋቁሙ ነው።

የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በአገራቸው እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ታንዛንያ በማቅናት ከፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ጋር የሁለቱን አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያና ታንዛንያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና በታንዛንያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ መጀመሩንም አውስተዋል።

አገሮቹ የፓን አፍሪካ እሳቤን በውጤታማነት የተገበሩና የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) መስራች እንደሆኑም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ "ሁለቱ አገሮች በጋራ መስራት የሚችሉባቸውን ዘርፎች በማስፋት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሩን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

"የኢትዮጵያና የታንዛንያ ባለሀብቶች በየአገራቱ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ማጎልበት ይችላሉ" ብለዋል።

በመጪው መጋቢት ወይም ሚያዚያ ወር ኢትዮጵያና ታንዛንያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚሰራ የጋራ ኮሚሽን እንደሚያቋቁሙ አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ አገሮቹ የፈረሟቸውን ስምምነቶች ተፈጻሚነት በመገምገም ምክረ ሀሳብ እንደሚያቀርብም ገልጸዋል።

የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ የስዋሂሊ ቋንቋ ትምህርት በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ ያቀረቡት ሃሳብ እንዳስደሰታቸውም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ከታንዛንያ የስዋሂሊ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራንን ለመቀበል ዝግጁ ናት፤ ምክንያቱም ስዋሂሊ በአፍሪካ ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው" ብለዋል።

ታንዛንያ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመፍታት ያላት ፍላጎትንም አድንቀዋል።

የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በበኩላቸው አገራቸው የሁለትዮሽ ትስስሩን የማጎልበት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በህገ ወጥ መንገድ ገብተው እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

"ኢትዮጵያና ታንዛንያ ባላቸው የቁም እንስሳት ሀብት ከአፍሪካ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያ ይህን ሃብቷን ተጠቅማ የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ተጠቃሚ እየሆነች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ታንዛንያ ባላት የቁም እንስሳ ሀብት በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ እንዳልሆነችና በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ያላትን ተሞክሮ መቅሰም እንደምትፈልግ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም