በምዕራብ አርሲ ዞን በ3 ሺህ 570 ሄክታር መሬት ስንዴ በመስኖ እየለማ ነው

84

አዲስ አበባ ጥር 17/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ አርሲ ዞን በ3 ሺህ 570 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እየለማ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የኢዜአ የጋዜጠኞች ቡድን በዞኑ አዳባ፣ ነገሌ አርሲ እና ሄበን አርሲ ወረዳዎች በመገኘት በመስኖ እየለማ ያለውን የስንዴ ማሳ ጎብኝቷል።

የዞኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዳላ ኢብራሂም በዞኑ በመጀመሪያ ዙር የመስኖ ልማት 3 ሺህ 958 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን ገልፀዋል።

በዚሁ መሰረት 3 ሺህ 570 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ተሸፍኗል፤ በዞኑም ከስንዴ ልማቱ 296 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።

አቶ አብደላ እንዳሉት ለአርሶ አደሮች የመስኖ ስንዴ አመራረት ስልጠና የተሰጠ ሲሆን በግብርና ባለሙያዎችም ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል። 

"ባለፈው ዓመት ስንዴ በመስኖ ካለሙ አካባቢዎች ልምድ በመውሰድ ከታቀደው በላይ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየሰራን ነው" ብለዋል።

አቶ አብደላ በሁለተኛ ዙር 5 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማና በመስኖ ልማቱ በድምሩ 8 ሺህ 958 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

የሄበን አርሲ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ገመቹ ቡላ ስንዴ በመስኖ ሲያለሙ የመጀመሪያቸው መሆኑን ገልጸው፤ ያለሙት ስንዴ ቡቃያ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

"የቡቃያው አያያዝ በክረምት ሳለማ ከነበረው ስንዴ የተሻለ በመሆኑ በመስኖ ካለማሁት ጥሩ ምርት አገኛለሁ የሚል ተስፋ አለኝ" ነው ያሉት።

የአዳባ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር መርጋ ጎበን በበኩላቸው ከግብርና ባለሙያዎች የተሰጣቸውን ምክር በአግባቡ በመተግበር የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ከመንግስት የስንዴ ዘር በነጻ እንደተሰጣቸውና ለመስኖ ልማቱ የአፈር ማዳበሪያ በአግባቡ መጠቀማቸውን ገልፀዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የግብርና ባለሙያዎችም አርሶ አደሩ መጀመሪያ አካባቢ ስንዴ በመስኖ ለማልማት ጥርጣሬ እንደ ነበረው አውስተዋል።

የአዳባ ወረዳ ግብርና ልማት ባለሙያ አቶ መሃመድ ሁሴን አርሶ አደሩን በማሰልጠን በክላስተር የማደራጀት ሥራ በመሰራቱ ጥርጣሬው መወገዱን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ግብዓት በወቅቱ በማቅረብ ምርትና ምርታነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ወደ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ከመገባቱ በፊት በቅድሚያ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ የማሳደግና የማሰልጠን ስራ መከናወኑን የገለፁት ደግሞ የኤባን አርሲ ወረዳ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ገለቶ ናቸው።

ስንዴና አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በዞኑ በአጠቃላይ 23 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑ ታውቋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም