ለምርት ዘመኑ ከ18 ሚሊዮን 100ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው... ግብርና ሚኒስቴር

47

ባህርዳር፤ ጥር 17/ኢዜአ/ በሀገር ደረጃ ለ2013/2014 የምርት ዘመን በግብአትነት የሚውል ከ18 ሚሊዮን 100ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ  በግብዓት አቅርቦት ዙሪያ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ በባህርዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ በሚኒስቴሩ የግብዓት ምርት ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ እንደገለጹት ግብርና  የሀገሪቱ  የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው።

ዘርፉን  ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የመደገፍና ግብዓት የማሟላት ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም ለ2013/2014 የምርት ዘመን ከ18 ሚሊዮን 100ሺህ  ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከታህሳሥ 27/2013 ዓ.ም ጀምሮ ማዳበሪያ ከውጭ ግዥ በመፈፀም ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ  መሆኑን ጠቅስው፤ እስከ አሁንም ከ2 ሚሊዮን 100ሺህ  ኩንታል በላይ ለህብረት ሥራ ማህበራት እየተከፋፈለ ይገኛል ብለዋል።

የአፈር ማዳበሪያው ያለ ምንም መስተጓጎል በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ደርሶ ጥቅም ላይ እንዲውልም በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል።

ለዚህም መሳካት  ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተሰጣቸው ኃላፊነት ልክ ተግባሩን እንዲወጡም አሳስበዋል።

ዛሬ በተጀመረው የምክክር መድረኩ የፌደራል፣ ክልል፣ ዞን አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም ዩኒየኖች እየተሳተፉ መሆኑን ሪፖርተራችን ከባህርዳር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም