ቀጥታ፡

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድንና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ሸለመች

አዲስ አበባ ሃምሌ 17/2010 የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም እንዲመጡ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከፍተኛ የክብር ሽልማት አበረከተች። የኢትዮጵያ፣ኤርትራና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሶስትዮሽ ስብሰባቸውን በአቡዳቢ እያካሄዱ ነው። የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አልጋወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከነበሩበት ሰላምና ጦርነት አልባ ግንኙነት ወጥተው ወደ ሰላምና ትብብር መምጣታቸውን አድንቀዋል። አልጋወራሹም መሪዎቹ ላደረጉት ጥረት የአገሪቱን ከፍተኛ የሲቪል ሽልማት ሚኒስትሮች፣አምባሳደሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ሸልመዋቸዋል። በሶስትዮሽ ውይይቱ ላይ የሶስቱ ሀገራት የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲሁም ቀጠናዊ ጉዳዮች ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያና የኤርትራ በድጋሜ የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከራቸው እንደምትደግፍ አልጋወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸያን ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትላንት በሳውዲ አረቢያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በአቡዳቢው የኢትዮጵያ፣ኤርትራና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሶስትዮሽ ውይይትን እየተሳተፉ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ለዚሁ ስብሰባ ዛሬ ወደ ስፍራው አቅንተው የሶስትዮሽ ስብሰባውን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም