በሠላም ግንባታ የቅድመ መከላከል ስርዓት በመዘርጋት ፍትሕን ለሁሉም ማረጋገጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሠላም ግንባታ የቅድመ መከላከል ስርዓት በመዘርጋት ፍትሕን ለሁሉም ማረጋገጥ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2013(ኢዜአ) ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥ በሠላም ግንባታ የቅድመ መከላከል ስርዓትን በመዘርጋት ፍትህን ለሁሉም ማኅብረሰብ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ።
በድህረ-ግጭት አያያዝ፣ በሕግ የበላይነትና በመልሶ ግንባታ የሠላም ምህንድስና ሚና ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች፣ የፌዴራልና የክልል ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በውይይት መድረኩ በድህረ-ግጭት አያያዝ፣ በሕግ የበላይነትና በመልሶ ግንባታ ላይ ያተኮሩ የመነሻ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከግጭት ክስተት በኋላ የተገኘን ሠላም ቀጣይ በሆነ መሠረት ላይ የማኖር ሂደትና ዳግም ግጭት እንዳይከሰት አስተማማኝ የመከላከል ሥርዓት መዘርጋት በሠላም ግንባታ ዙሪያ ሊተኮርበት እንደሚገባም ተነስቷል።
ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ ችግሮችን ከመሰረቱ ማረም ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ላይ እንዲሰራም ተጠቁሟል።
በድህረ ግጭት የተጎዱ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የፀጥታና የፖለቲካ ተቋማት መልሰው የሚገነቡበትን ሂደት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ቧያለው የውይይት መድረኩን ጠቀሜታ ገልጸዋል።
በመድረኩ በድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ ጸጥታ መጠበቅ፣ ፍትህና እርቅ ማስፈን፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ማረጋገጥና አሳታፊ የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋት ዋነኛ የሠላም ምሰሶዎች መሆናቸው ተገልጿል።
የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥ በሠላም ምህንድስና የቅድመ መከላከል ስርዓት በመዘርጋት ሠላምን ማሳደግና ፍትህን ለሁሉም ማረጋገጥ እንደሚገባ አንስተዋል።
ለዚህም "የሠላም ምህንድስና ምሰሶዎች የሆኑትን የግጭት ጥልቅ ትንተና፣ ተቋማዊ መዋቅራዊ ማዕቀፍ፣ የሠላም መሰረተ ልማት ግንባታና የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ይገባል" ብለዋል።
ግጭትን መቀነስ፣ የሠላም ባሕልን ማዳበር እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሠላም መሰረተ ልማት ግጭትን ለመከላከልና ሠላምን የሚያጎለብቱ ተቋማትን ለመገንባት አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው ተመሳሳይ ውይይቶች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት የአገሪቷን የውጭ ግንኙነት በምርምርና ጥናት የመደገፍ ሥራ ይሰራል።
በኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት ይበልጥ እንዲጎለብት የሚያግዙ የግንዛቤና የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥም ይታወቃል።