ፌዴሬሽኑ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ የተመጣጠነ እንዳልሆነ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴሬሽኑ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ የተመጣጠነ እንዳልሆነ ተገለጸ
መቀሌ ግንቦት 4/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የክልሉ የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ አስታወቁ። ፌዴሬሽኑና ቢሮው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የቅጣት ውሳኔው አስተማሪ ያልሆነና ዘንድሮ ሊጉን በተቀላቀለው ክለብ ላይ የራሱን ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው። የትግራይ ክልል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሕሸ ለማ እንደገለጹት በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ጥፋቶች ባደጉ ሃገራት ክለቦችም ሊከሰት የሚችል ሆኖ ሳለ የተጋነነ ቅጣት ማሳለፍ ስፖርቱን የሚጎዳ ነው። ፌዴሬሽኑ የክለቡ ቡድን መሪ ላይ ያስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ የሚደገፍ ቢሆንም በተጨዋቾች ላይ የተሰጠው ቅጣት ፍትሃዊነትን ታሳቢ ያላደረገና የክለቡ ህልውና ላይ የከፋ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑንም ተናግረዋል። በመሆኑም የክልሉን እግር ኳስ እድገትና የስፖርቱን አፍቃሪ ህብረተሰብ ታሳቢ ባደረገ መልክ ውሳኔው እንደገና እንዲታይ ጠይቀዋል። "የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ክለቡ ለኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ አዲስ በመሆኑ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ተሰጥቶት መታረም ነበረበት" ያሉት ደግሞ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ አቶ ነጋ አሰፋ ናቸው። "የቅጣት ውሳኔው ክለቡን የሚያፈርስና የሃገራችንን የእግር ኳስ ስፖርት የሚያጨልም ነው" ሲሉ የቢሮው ሃላፊ አስታውቀዋል። ክለቡ በዕለቱ የተከሰተውን ችግር አምኖበት ተገቢውን የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ የስፖርቱን ማህበረሰብ ይቅርታ መጠየቁን ተናግረዋል። ፌዴሬሽኑ ክለቡ የወሰዳቸውን የእርምት እርምጃዎች ግምት ውስጥ ያላስገባም በመሆኑ ውሳኔው እንደገና እንዲታይ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ የውልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን መሪን ለእድሜ ልክ ያገዳቸው ሲሆን ሰባት የክለቡ ተጫዋቾች ላይ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ እገዳና ከ10 ሺህ ብር እስከ 15 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት አስተላልፏል። ከዚህ በተጨማሪም ክለቡ እንደ ክለብ 250 ሺህ ብር እንዲቀጣና ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።