ካውንስሉ የትምህርትን ጥራት በማስጠበቅ የብልጽግናውን ጉዞ የማፋጠን ፋይዳ አለው - ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ

71

አዲስ አበባ፣ ጥር 15/2013 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ካውንስል የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ በማፋጠን የራሱ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገለጸ።

ካውንስሉ ሁለተኛ ጉባዔውን ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካሄዷል።

በጉባዔው የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ካውንስሉ የትምህርት ጥራት ክፍተቶችን ከመለየት ባሻገር ጥራቱን ለማስጠበቅ ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉባዔው የሚወጡ የምርምር ጥናቶች ለኅብረተሰቡ የሚኖራቸውን ፋይዳ በመመርመር በተግባር ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮችን በሚገባ የመጠቀም ልምድ እምብዛም መሆኑን አውስተው "የሃገር ሃብት የወጣባቸውን ምሁራን እውቀት መጠቀም ከተቻለ የትምህርትን ጥራት ማሳደግ ይቻላል" ብለዋል።

ቁጥራቸው 40 ሺህ የሚጠጋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን መኖራቸውን ያመለከቱት ሚኒስትሩ የፕሮፌሰሮች ካውንስል የእነዚህን መምህራን አቅም በመገንባት ጭምር ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ይህም የትምህርትን ጥራት በማስጠበቅ እንደ አገር ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ በማፋጠን በኩል የራሱ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።

እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለጻ ብዙ ወጪ የሚጠይቀውን የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት በተመጣጣኝ ክፍያ መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ከካውንስሉ የሚገኘው ምክረ ሀሳብ ፋይዳው የላቀ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የካውንስሉ ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው አገሪቷን ካለችበት ችግር በማውጣት በብልጽግና ለማስቀጠል ከምሁራን ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

የፕሮፌሰሮች ካውንስሉ ውይይት ሲያካሄድ ሁለተኛው መሆኑን ጠቁመው፣ በምሁራኑ የሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦችን በመቀበል ወደ ተግባር መቀየር የመንግስት ሚና እንደሆነ አመልክተዋል።

በመሆኑም "በሳይንስ የተደገፉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ወደ ተግባር ለመቀየር መንግስት ከካውንስሉ ጋር ተቀራርቦ መስራት አለበት" ነው ያሉት።

ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቅ በበኩላቸው ካውንስሉ ለመንግስት የተደራጀ አካልን በአግባቡ እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርለት ገልጸዋል።

ምሁራንም አገሪቷን ወደ ብልጽግና በሚያራምዱ ሃሳቦች ላይ በጋራ ለመምከር የሚያስችላቸው መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

አያይዘውም "የካውንስሉ መመስረት አገሪቷ ለእውቀት ዋጋ መስጠቷን የሚያመላክት አንድ እርምጃ ነው፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።

"ካውንስሉ ምሁሩ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ተምሬ አገሬን ልጠቅም ይገባኛል ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል" ሲሉ የገለጹት ፕሮፌሰር ያለው የትምህርትን ጥራት በማረጋገጥ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ካውንስል ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 230 ፕሮፌሰሮችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ተመስርቶ ወደ ሥራ መግባቱን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም