በሲዳማ ክልል ግንባታቸው የተጠናቀቁ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

ሐዋሳ፣ ጥር 15/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ግንባታቸው የተጠናቀቁ የመንገድ፣ ድልድዮች እና ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት የተመረቁት ፕሮጀክቶች 380 ኪሎ ሜትር ጥርጊያና የጠጠር መንገድ፣ዘጠኝ ድልድዮችና አራት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ናቸው።

ርዕሰ መስተዳድሩ ትናንት በተከናወነው የምረቃ ሥነ- ሥርዓት ወቅት እንዳሉት በክልሉ ከመዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የሠላም መደፍረስ ባለፉት አራት ዓመታት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ትኩረት ተነፍጓቸው ቆይቷል።

ጥያቄው ምላሽ አገኝቶ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ወደ ልማት በመዞር የተጓተቱ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ እንደ ሃገር የልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ የማስፈጸም አቅምን በማዳበር ቀሪ ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የክልሉ የውሃና መስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ውብሸት ፀጋዬ በበኩላቸው የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል 15 የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ቢጀመርም ለአምስት ዓመታት መጓተቱን አውስተዋል።

ለፕሮጀክቶቹ መጓተት በዋናነት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ፣ የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ፣ የውጭ ምንዛሪ መዋዠቅና የተቋራጮች አቅም ውስንነትን ጠቅሰዋል።

የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ በመመድብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም እንቅስቃሴ በቦርቻና ዳሌ ወረዳዎች 26 የውሃ ማከፋፊያ ቦኖዎች ያላቸው አራት የውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አሰታውቀዋል።

በተጠናቀቁት የውሃ ተቋማት 30 ሺህ የሚጠጉ የአከባቢው ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ቀሪዎችንም የውሃ ፕሮጀክቶች እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ የተጠናቀቁትና ግንባታቸው በሂደት ላይ የሚገኙት ሁሉም ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ስራ ሲጀምሩ የክልሉን የመጠጥ ውሃ ሽፋን አሁን ካለበት ከ38 በመቶ ወደ 46 በመቶ ያሳድገዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በ321 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ1 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ የጥርጊያና የጠጠር መንገድ እንዲሁም 49 መለስተኛ ድልድዮች ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ለታሞ ናቸው።

ከእነዚህም ዘጠኝ ድልድይና 380 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት መብቃታቸውን አመልክተዋል።

በክልል የቦርቻ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ዝናሬ ቲቦ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው የንጹህ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ወራጅ ውሃ ለመጠቀም በመገደዳቸው ለውሃ ወለድ በሽታ ሲጋለጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ንጽህናው ያልተጠበቀ አንድ ጀሪካን ውሃ በ10 ብር ለመግዛት ይገደዱ እንደነበረና አሁን የተሰራው የውሃ ተቋም ችግራቸውን በማቃለሉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በርዕሰ መሰተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ የተመራው የክልሉ ሉዑካን በሲዳማ የተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄዱ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችንም እንቅስቃሴ በመስክ ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም